(ፓሪስ) የሰብአዊ መብት ተሟጋቹ ድርጅት ሂውማን ራይትስ ዎች እንዳለው በፈረንሳይ ካሌይ የስደተኞች መጠለያ ፖሊሶች በጥገኝነት ጠያቂዎችና ሌሎች ስደተኞች ላይ በተደጋጋሚ የሰብአዊ መብት ጥሰት እየፈፀሙ ነው፤ መንግስትም ለሚቀርቡ አቤቱታዎች መፍትሔ ከማፈላለግ ይልቅ ዝምታን መርጧል።
“በገሀነብ እንደመኖር፤ በሕፃናትና ጎልማሳ ስደተኞች ላይ በፖሊሶች የሚፈፀሙ ጥቃቶች፤ በካሌይ” በሚል በወጣ ባለ 41 ገፅ ሪፖርት ሀተታ መሰረት በካሌይ ያሉ ፖሊሶች በተለይም ደግሞ የፈረንሳይ አድማ በታኝ ፖሊሶች በራሳቸውም ሆነ በሌሎች ላይ ምንም አደጋ በማይጋርጥ ሁኔታ ውስጥ ባሉ ሕፃናትና ጎልማሳ ስደተኞች ላይ በተደጋጋሚ ፔፐር ስፕሬይ ተጠቅመዋል። ፖሊሶቹ እንቅልፍ በተኙ ስደተኞች ላይ ብቻ ሳይሆን ስደተኞቹ በሚመገቡት ምግብና በሚጠጡት ውኃ ላይም ጭምር ፔፕር ስፕሬይ ረጭተዋል ነው የተባልው። ሕፃናትና ጎልማሳ ስደተኞቹ አካባቢውን ለቀው እንዲሄዱ ለማስገደድ በሚደረግ ጥረትም ፖሊሶቹ በተገኘው አጋጣሚ ሁሉ ስደተኞቹ ለመተኛና መጠለያ የሚጠቀሙባችውን አልባሳትና ቁሳቁሶች ይወርሳሉ። በሪፖርቱ መሰረት እነዚህ ድርጊቶች ሰብአዊነት የጎደላችውና ከዓለም አቀፉ የፖሊስ አሰራር መመሪያ ደንብን የሚፃረሩ ናቸው። በዓለም አቀፉ የፖሊስ አሰራር መመሪያ ደንብ መሰረት ፖሊስ ኃይል መጠቀም የሚችለው በአስገዳጅ ሁኔታዎች ውስጥ ብቻ ሲሆን የሚወሰደውም እርምጃ ለተፈጠረው ችግር ተመጣጣኝና ህግና ደንብን ለማስከበር ብቻ መሆን አልበት።
“በተኙ ህፃናት እና ጎልማሶች ላይ ወይንም የቀን ኑሮዋቸውን በሰላም እየኖሩ ያሉ ስደተኞች ላይ ፔፐር ስፕሬይ መርጨት ሊኮነን የሚገባው አሳፋሪ እርምጃ ነው ብለዋል:: የፈረንሳይ የሂዩማን ራይትስ ዎች ዳይሬክተር ቤኔድክት ዤኔሮድ። ኃላፊው አክለውም “ፖሊሶች የስደተኞችን ብርድልብስ፣ ጫማ እና ምግብ ሲነጥቁ ወይንም ሲያበላሹ የፖሊስ ሞያቸውን ክብር እያሳጡ እና መብቱን እንጠብቃለን ብለው ቃል የገቡለትን ህዝብ እየጎዱ ነው” ብለዋል ።
በሰኔ እና በሐምሌ 2017 በተሰናዳው ሪፖርት ከ60 በላይ የሚሆኑ የፖለቲካ ጥገኝነት ጠያቂዎች፣ ካሌይና ዳንኬርክ የሚኖሩ ስደተኞች እንዲሁም 31 የሚጠጉ ብቻችውን የተሰደዱ ሕፃናት ተካተዋል። በተጨማሪም ሂዩማን ራይትስ ዎች ይህንን ሪፖርት ለማጠናከር እንዲረዳው በሚል በፓሪስ፣ ካሌይና ዳንኬርክ ያሉ ጉዳዩ የሚመለከታቸውን የመንግስትና መንግስታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች ሰራተኞችን አነጋግሯል።
ከ400 በላይ ከለላ ፈላግዎች እና ሌሎች ስደተኞች በአብዛኛው ከኤርትራ፣ ከኢትዮጵያ እና ከአፍጋንስታን የመጡ ስደተኞች በካሌይ ጎዳናዎች እና ጫካ ውስጥ እየኖሩ ነው። ከነዝህ ውስጥ የቤተሰብ ከለላ የሌላቸው ሕፃናት 200 ይሆናሉ። ከ300 የማያንሱ ህፃናት እና ጎልማሶች በአብዛኛው የኢራቅ ኩርዱዎች፣ አፍጋኖች እና የሌላ ሀገር ዜጎች በምስራቅ ካሌይ በዳንኬርክ፣ በግሮንሳንቲ እና አካባቢው ባሉ የስደተኞች መጠለያዎች ውስጥ እየኖሩ ነው።
የካሌይ ምክትል አስተዳዳሪ በሪፖርቱ በፖሊስ ደረሱ የተባሉት የሰብአዊ መብት ጥሰቶች መሰረተቢስ ውንጀላዎች ናቸው ቢሉም ሂዩማን ራይትስ ዎች ግን ሪፖርቱ ስደተኞቹ እና ከለላ ፈላጊዎቹ ደረሰብን ያሉትን ቃል በቃልና በዝርዝር ያካተተነው በማልት ይሞግታል።
የካሌይ ባላስልጣናት ስደተኞች ወደ ስደተኞች መጠለያው ሲመለሱ ምግብ፣ ውሃ እና ሌሎች መሰረታዊ ፊላጎቶች እንዳያገኙ እንቅፋት እየፈጠሩ መሆናቸውን ሂዩማን ራይትስ ዎች ደርሼበታልሁ ብሏል።።
የዕርዳታ ቡድኖች መሰረታዊ ፊላጎቶችን እንዳያከፋፍሉ የካሌይ አስተዳደሪዎች እየፈጠሩት ያለው አንቅፋት ስደተኞቹ ኢሰብአዊ እና የሰውን ክብር ዝቅ በሚያደርግ ሁኔታ እንዲኖሩ ምክንያት ነው በማለት በመጋቢት ወር ኣንድ የፈረንሳይ ፍርድ ቤት ውሳኔ አስተላልፏል። የፈረንሳይ ዕምባ ጠባቂ ተቋምም ይሄን እና ሌሎች የካሌይ አስተዳዳሪዎች የወሰዱትን እርምጃውች በመንቀፍ በከሌይ የሚገኙ ስደተኞች እና ከለላ ፈላጊዎች ሰብአዊነት በጎደለው ሁኔታ እንዲኖሩ እያደረገ ነው በሚል ተችቿል።
በሰኔ 26 የተላለፈው ሁለተኛው የፍርድ ቤት ውሳኔ የአከባቢው አስተዳዳሪዎች ለስደተኞች የመጠጥ ውሃ፣ የመጸዳጃ ክፍል እንዲሁም የገላ እና የልብስ ማጠብያ ግልጋሎቶችን በ10 ቀን ውስጥ እንዲያሟሉ አዞ ነበር። የካሌይ አስተዳዳሪዎች ትዕዛዙን ላለመቀበል ሓምሌ 6 ይግባኝ ጠይቀዋል። ፍርድ ቤቱም አቤቱታውን ለማድመጥ ለሓምሌ 28 ቀነ ቀጠሮ ተይዟል።
የ17 ዓመቱ ብንያም ተ. ለሂዩማን ራይትስ ዎች እንደገለጸው “በተኛንበት ካገኙን አቃጣይ ፔፐር ስፕሬይ ይረጩብንና ንብረቶቻችንን ሰብስበው ይወስዱብናል። በየሁለት-ሦስት ቀን እየመጡ እንደዚህ ያደርጋሉ። ብርድ-ልብሳችንንም ይወስዱብናል።”
በአንድ አጋጣሚም የዕርዳታ ሰራተኞች ከባድ መሳሪያ በታጠቁ የጸጥታ ሀይሎች መከበባቸውን እና ስደተኞች የዕርዳታ ሰረተኞችን እንዳያገኙ በተደጋጋሚ በመከልከል እና ከእጃቸው ምግብ እየነጠቁ ሲጥሉ እንደነበረም ነው የተናገረው።
የእርዳታ ሰራተኞቹ የፖሊሶቹን ድርጊት ለማስረጃነት በስልኮቻቸው ፎቶና ቪድዮ ለመቅረፅ ቢሞክሩም ያለ ምንም የህግ አግባብ ስልኮቻችውን በፖሊሶች መነጠቃቸውን ብሎም ስልኮቹ ተበረበረው መረጃዎችን መጥፋታቸውን ነው ዓይን እማኞች የተናገሩት።
እስከ 2016 ጥቅምት ወር መጨረሻ ድረስ በከተማዋ ዳር ላይ ባሉ እጅግ በቆሸሹ እና በተጎሳቆሉ መንደሮች ውስጥ ብዙ ህፃናትን ጨምሮ ቢያንስ 10,000 ከለላ ፊላጊዎች እና ስደተኞች ይኖሩ ነበር። የካሌይ ባለስልጣናት በከተማዋ ዙሪያ የስደተኞች ካምፕ ዳግም እንዳይሰራ የተቻላቸውን ሁሉ እንደሚያደርጉ በተደጋጋሚ ሲግልፁ ቆይተዋል።
በርካታ ስደተኞች ከሰሜን ፈረንሳይ ወደ ካሌይ እንዳይፈልሱ በሚል ሰበብ የአካባቢው ባለስልጣናት በከተማይቱ ደረጃቸውን የጠበቁ የስደተኛ መጠለያዎችም ሆነ የስደተኛ ጉዳይ ቢሮዎች እንዲከፈቱ ሲደረግላቸው የነበረውን ጥሪ በተደጋጋሚ ውድቅ ማድረጋቸው ይታወሳል። ሰኔ 23, 2017 የውስጥ ጉዳይ ሚንስተሩ ዤራር ኮሎም ካሌይን ሲጎበኙ ይሄንን አመላካከት አንጸባርቀዋል።
ፕሬዘዳንት ኢማኑኤል ማክሮንም ወገናዊነትና ሰብአዊነትን ያማከለ የስደተኞች አያያዝ ስርዓትን ተግባራዊ ለማድርግ ቃል ገብተው ነበር። በሓምሌ ወር መጀመሪያ በትሬስቴ ጣልያን በተከሄደው የአውሮፓ ህብረት ስብሰባ ላይ ፕሬዝዳንት ማክሮን “በፊት ከሶሪያ ሲመጡ የነበሩ ሰዎች አሁን አሁን ከኤርትራ እና ለነጻነት ከሚታገሉ ሌሎች ሀገሮች ነው የሚመጡት። እነዚህን ሰዎች አውሮፓ በተለይም ፈረንሳይ ልትቀበላቸው ይገባል። ስለዚህ እኛም በጉዳይዩ የድርሻችንን እንወጣለን።’’ ብለዋል።
በከተማም ሆነ በአገር አቀፍ ደረጃ የሚገኙ ባለስልጣናት ማንኛውም የፖሊስ ኃይል አባል ለዓለም አቀፉ የፖሊስ ሰነምግባር ደንብ መመሪያ እንዲገዛና የእርዳታ ስራዎችን ከማስተጓጎል እንዲቆጠብ፤ ይህንን ተግባራዊ በማያደርጉ ላይ ስልጣንን ያለ አግባብ ተጠቅመዋል በሚል ተመጣጣኝ የሆነ የማያዳግም እርምጃ ቢወስዱ ለችግሩ መፍትሔ ሊሆን እንደሚችል ሂዩማን ራይትስ ዎች አመላክቷል። ማዘዝ እርዳታን የማድረሱ ተግባር ያለ አንዳች እንከን በሰላማዊ መንገድ እየተከናወነ ባለበት ሁኔታ ውስጥ ተገቢ አይደልም ይላል ድርጅቱ።
የውስጥ ጉዳይ ሚንስተር የስደተኞች ከለላን የሚያደናቅፉ ነገሮችን በአስቸኳይ ማስወገድ አለበት። የጥገኝነት ቢሮን በካሌይ በመክፈት ወይንም በነባር ቢሮዎች የጥገኝነት ማመልከቻ ማስገባት የሚቻልበትን ሁኔታ ማመቻቸት አለበት። በካሌይ ያለመጠለያ ለሚኖሩት ከለላ ፈላጊዎች በተቻለ ፍጥነት መኖሪያ ለመስጠት እና ሌሎች ስደተኞችም ግዜያዊ መጠለያ እንዲኖራቸው የሚንስቴር መስሪያ ቤቱ ከሚመለከታቸው ኤጀንሲዎች እና ሰብአዊ ቡድኖች ጋር መስራት አለበት ነው ያለው ድርጅቱ።
የአከባቢው ሆነ የሀገሪቱ ባለስልጣናት የቤተሰብ ጥበቃ የሌላቸው ስደተኛ ህፃናት በቂ መጠለያ እና ድጋፍ ሰጪ ሰራተኞችን ያካተታ የከለላ አገልግሎት ማግኘታቸውን ማረጋገጥ አለባቸው ብሏል ድርጅቱ።።
“ፓሊሶች በስደተኞች ላይ የሚያደርሱትን ጥቃት እና ትንኮሳ እንደማይታገሱ ለፖሊሶች ግልጽ መልክት ማስተላለፍ አለባቸው” ብለዋል ሚስተር ዤኔሮድ። አክለውም “መንግስት ስደተኞች ህጋዊ ከለላ ማግኘታቸውን እና ጥገኝነት ለመጠየቅ መቻላቸውን ማረጋገጥ አለበት” ብለዋል።
“በገሀነብ እንደመኖር፤ በሕፃናትና ጎልማሳ ስደተኞች ላይ በፖሊሶች የሚፈፀሙ ጥቃቶች፤ በካሌይ” ሙሉ ዘገባ እዝህ ጋር ያገኙታል።