(ናይሮቢ) – በጥቅምት ወር 2012 ዓ.ም. የብዙዎችን ህይወት በቀጠፈው ግጭት ላይ ምርመራ ከማካሄድ እና ለወደፊቱ ተመሳሳይ ጥቃቶች በጸጥታ ሀይሎች እንዳይፈጸሙ እና በማህበረሰቦች መካከል ተመሳሳይ ግጭቶች እንዳይከሰቱ ለመከላከል የሚያስችሉ እርምጃዎችን ከመውሰድ አንጻር የኢትዮጵያ መንግስት የወሰዳቸው እርምጃዎች አጥጋቢ ያለመሆናቸውን ዓለም አቀፉ የሰብዓዊ መብት ጥበቃ ድርጅት በዛሬው ዕለት ገለጸ። ግጭቱ ከተፈጠረ ስድስት ወራት ያለፉ ቢሆንም በኦሮሚያ ክልል ሁለት ከተሞች ውስጥ የሚኖሩት የግጭቱ ተጎጂዎች እና ቤተሰቦቻቸው በጸጥታ ሀይሎች እና በነውጠኞች ለተፈጸመባቸው ጥቃት አሁንም ፍትህ አላገኙም።
አንጋፋው አክቲቪስት ጃዋር መሀመድ ባለስልጣን አካላት ጠባቂዎቼን አስፈራርተዋል በማለት በማህበራዊ ሚዲያ ላይ ያስተላለፋቸውን መልዕክቶች ተከትሎ ጥቅምት 12 ቀን የኢትዮጵያ ዋና ከተማ የሆነችው አዲስ አበባ በተቃውሞ ሰልፎች የተናጠች ሲሆን ፖሊስ የጃዋርን ውንጀላ አስተባብሏል። በኦሮሚያ እና ሀረር ክልሎች ውስጥ ወደሚገኙ ከአሥር በላይ የሚሆኑ ከተሞች እንዲሁም ወደ ድሬዳዋ ከተማ የተዛመተው ይህ የተቃውሞ ሰልፍ በተለያዩ ቦታዎች ወደ ያለመረጋጋት እና ማህበረሰባዊ ግጭት ሊቀየር ችሏል። መንግስት በይፋ እንደገለጸው ከሆነ ከጸጥታ ኃይሎች ጋር በተፈጠረ “ግብግብ” የተነሳ የሞቱ 10 ሠዎችን ጨምሮ በኦሮሚያ እና በዙሪያዋ ባሉ አካባቢዎች የተቃውሞ ሰልፎቹ እና ግጭቶቹ በተፈጠሩበት ወቅት 86 ሠዎች ህይወታቸው አልፏል።
የሰብአዊ መብት ጥበቃ የአፍሪካ ቀንድ ዳይሬክተር ሌቲቲያ ባደር “የኢትዮጵያ መንግስት በርካታ ቁጥር ባላቸው ሰዎች ላይ የተፈጸመውን ግድያ እና የአካል ጉዳት፣ በመኖሪያ እና በንግድ ቤቶች ላይ የደረሰውን ውድመት እና በሆስፒታሎች ውስጥ የተፈጸመውን ጥቃት አድበስብሶ ሊያልፈው አይችልም” ብለዋል። በተጨማሪም “መጪው ምርጫ ደህንነቱ እና ጸጥታው በተጠበቀ መልኩ መደረግ መቻሉን ለማረጋገጥ መንግስት በጥቅምት ወር በተፈጠረው ግጭት ላይ የሚያደርገውን ምርመራ ሊያፋጥን እና ጥቃቶችን የፈጸሙ ሰዎችን ለፍትህ ሊያቀርብ ይገባል” በማለት አክለዋል።
19 ጥቃቶች የደረሰባቸው ሰዎችን፣ የዓይን እማኞችን፣ የጤና ባለሞያዎችን እና የተጎጂዎች ቤተሰቦችን እንዲሁም 5 ጋዜጠኞችን፣ ምሁራንን እና የሰብዓዊ መብት ባለሞያዎችን ጨምሮ የሰብአዊ መብት ጥበቃ ከጥቅምት ወር እስከ ጥር ወር 2012 ዓ.ም. ድረስ በኦሮሚያ ክልል ማለትም ምዕራብ አርሲ ዞን ውስጥ በሚገኘው በዶዶላ እና ምዕራብ ሸዋ ዞን ውስጥ በሚገኘው በአምቦ ከ24 ሰዎች ጋር ቃለ መጠይቅ አድርጓል። ቃለ መጠይቆቹ የተደረጉት በስልክ በኦሮምኛ፣ በአማርኛ እና በእንግሊዝኛ ቋንቋ ነበር። በተጨማሪም የሰብአዊ መብት ጥበቃ የሳተላይት ምስሎችን የገመገመ ሲሆን እነሱም ዶዶላ ውስጥ በሚገኙ የመኖሪያ እና የንግድ ቤቶች ላይ ጥቃቶች ስለመፈጸማቸው ምስክሮች የሰጡትን ቃል የሚያረጋግጡ ናቸው።
አምቦ ውስጥ መጀመሪያ ላይ ሰላማዊ የነበሩ ኋላ ላይ ግን ድንጋይ መወርወር የጀመሩ የተቃውሞ ሰልፍ አድራጊዎች ላይ የኦሮሚያ ፖሊስ አስለቃሽ ጭስ እና ጥይት መተኮሱን የሰብአዊ መብት ጥበቃ ደርሶበታል። ጥቅምት 12 እና 13 ቢያንስ ስድስት የተቃውሞ ሰልፍ አድራጊዎች በጥይት ተመትተው መሞታቸውን እና 37 ሰዎች ደግሞ ጉዳት የደረሰባቸው መሆኑን የህክምና ባለሞያዎች እና የዓይን እማኞች ገልጸዋል። በአምቦ በተደረጉት የተቃውሞ ሰልፎች ወቅት ህይወታቸው ያለፈ የጸጥታ ሀይሎችም እንደነበሩ የፌዴራል ጠቅላይ አቃቤ ሕግ ጽ/ቤት ከሰብአዊ መብት ጥብቃ ለቀረበለት ጥያቄ በጽሁፍ በሰጠው ምላሽ ገልጿል።
አምቦ ውስጥ የነበሩት የተቃውሞ ሰልፎች በፍጥነት መጥፎ አቅጣጫ ሊይዙ የቻሉት የኦሮሚያ ፖሊስ የተቃውሞ ሰልፍ አድራጊዎች ላይ ተኩስ ከከፈተ በኋላ እንደነበር አንድ የዓይን እማኝ ገልጸዋል። የዓይን እማኙ “መጀመሪያ ላይ ሰልፉ ሰላማዊ ነበር፣ ከዚያ ግን [አንድ የፖሊስ አባል] በአንድ ሰላማዊ ሰልፍ አድራጊ ላይ ጉዳት አደረሰ። የስምንተኛ ክፍል ተማሪ ነበረ። ከዚያም የተቃውሞ ሰልፍ አድራጊዎቹ ስሜታዊ ሆኑ። ማህበረሰቡ ፖሊስ ጥይት እንዳይተኩስ ሲጠይቅ ነበር። ከዚያ ግን [ከፖሊሶቹ ውስጥ] አንዳንዶቹ ሰላማዊ ሰልፍ አድራጊዎቹ ላይ መተኮስ ጀመሩ። ማህበረሰቡ የፖሊስ አባላቱን ያውቃቸዋል። ይህን ሲያደርጉ ማየት ልብን የሚሰብር ነገር ነበር” ብለዋል።
ዶዶላ ውስጥ ጥቅምት 12 እና 13 የተቃውሞ ሰልፎቹ ወደ ማህበረሰባዊ ግጭት ከተለወጡ በኋላ በከተማው ውስጥ ከሚኖሩት የተለያዩ ብሔረሰብ አባላት ውስጥ ቢያንስ 10 ሰዎች ተገድለዋል እንዲሁም 60 ሰዎች የአካል ጉዳት ደርሶባቸዋል። ነውጠኛ ቡድኖች በተቃውሞ ሰልፍ አድራጊዎች እና በነዋሪዎች ላይ ጥቃት የፈጸሙ፣ ንብረት የዘረፉ እና ሱቆችን እና የንግድ ቤቶችን ያቃጠሉ ሲሆን በዚህም የተነሳ በሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎች በቤተ-ክርስትያናት ውስጥ ለመጠለል ተገደዋል። በተጨማሪም ነውጠኛ ቡድኖች በዶዶላ ጠቅላላ ሆስፒታል በርካታ ታካሚዎችን እና ቤተሰቦቻቸውን ደብድበው ገድለዋል።
የዓይን እማኞች እንደተናገሩት ከሆነ በዶዶላ የሚገኙ የአካባቢው እና የክልሉ የጸጥታ ሀይሎች የምላሽ የሰጡት ዘግይተው ነበር ወይም በሆስፒታሎች ውስጥ ጨምሮ በነውጠኛ ቡድኖች ከተፈጸሙ ጥቃቶች ውጤታማ በሆነ መልኩ አልታደጓቸውም። ጥቅምት 13 ቀን አነስተኛ ቁጥር ያላቸው የፌዴራል መከላከያ ኃይል አባላት ወደ ዶዶላ የመጡ ሲሆን በከተማው በሚገኙት ሁለት ቤተ-ክርስቲያኖች ዙሪያ ሰፍረዋል። እነዚህ ወታደሮች የካቲት ወር መጨረሻ ላይ አካባቢውን ለቀው እንደሄዱ የዓይን እማኞች ገልጸዋል።
የኢትዮጵያ ባለሥልጣን አካላት ተፈጽመዋል የሚባሉ ጥቃቶች፤ በተለይም ደግሞ በጸጥታ ኃይሎች ተወስደዋል የሚባሉ ከመጠን ያለፉ የኃይል እርምጃዎች እና በነውጠኛ ቡድኖች በተፈጸሙ የጭካኔ ድርጊቶች ውስጥ በተሳተፉ ሰዎች የተፈጸሙ ጥቃቶች በገለልተኛ አካል ምርመራ ተደርጎባቸው በዓለም አቀፍ የፍትሀዊ ዳኝነት መለኪያ መሰረት በአግባቡ መቀጣታቸውን ማረጋገጥ እንዳለባቸው የሰብአዊ መብት ጥበቃ ገልጿል። ምርመራዎቹ የጸጥታ ኃይል አዛዦች በጥቃቶች ውስጥ ሚና በመጫወት፣ በጸጥታ ኃይል አባላት የተፈጸሙ ማናቸውንም ጥቃቶች ባለመከላከል ወይም ባለማስቆም እንዲሁም በነውጠኛ ቡድኖች የሚፈጸሙ ጥቃቶችን ባለመከላከል ያጠፏቸውን ጥፋቶች ማካተት ይኖርባቸዋል። መንግስት በጸጥታ ሀይሎች የተፈጸሙ ጥቃቶች ተጎጂዎች እና ቤተሰቦቻቸው ፈጣን እና ፍትሀዊ ካሳ ማግኘታቸውን ማረጋገጥ እንዲሁም የማህበረሰባዊ ግጭት ተጎጂዎች ካሳ እንዲያገኙ የሚያስችል ፕሮግራም መዘርጋት የሚለውን ጉዳይ ሊያስብበት ይገባል።
ጥቃቶቹ ከተፈጸሙ በኋላ ብዙም ሳይቆይ የክልል እና ፌዴራል ባለስልጣን አካላት አንዳንድ ሰዎችን በቁጥጥር ስር እንዳዋሉ እና ምርመራዎች በመከናወን ላይ መሆናቸውን ገልጸው ነበር። የፌዴራል ጠቅላይ አቃቤ ሕግ ጽ/ቤት የካቲት 13 ቀን ለሰብአዊ መብት ጥበቃ በጻፈው ደብዳቤ የፌዴራል እና የክልል ባለስልጣን አካላት በአምቦ እና በዶዶላ በጋራ ምርመራ አከናውነዋል በማለት ምላሽ ሰጥቷል። የጠቅላይ አቃቤ ሕግ ጽ/ቤት አምቦ ውስጥ ምርመራዎች በሂደት ላይ መሆናቸውን እና በዶዶላ ውስጥ ደግሞ የተጠናቀቁ መሆኑን፣ በ12 ሠዎች ላይ ክስ የተመሰረተ መሆኑን እና ክሳቸው በመሰማት ላይ መሆኑን ገልጿል። ነገር ግን ክስ የተመሰረተባቸው ሰዎች እነማን እንደሆኑ እና የተከሰሱባቸው ወንጀሎች ምን እንደሆኑ፣ ስንት ተጠርጣሪዎች በቁጥጥር ስር እንደዋሉ እና የፍርድ ሂደቱ በዜና ለህዝብ የሚዘገብ እንደሆነ በይፋ የተነገረ ምንም መረጃ እንደሌለ የሰብአዊ መብት ጥበቃ ገልጿል።
“የኢትዮጵያ መንግስት ለጥቃቱ የሰጠው በቂ ያልሆነ ምላሽ ሰው የሞቱባቸው እና ያላቸውን ሁሉ ያጡ ሰዎችን ስቃይ የሚያባብስ ነው” ብለዋል ባደር። በተጨማሪም “ምርጫ 2012 በመቃረብ ላይ ባለበት በአሁኑ ወቅት በጸጥታ እና በፍትሕ ሥርዓቱ ላይ ህዝቡ ያለውን እምነት ማጠናከር ሁኔታዎች እንዳይቀጣጠሉ በመከላከል ረገድ ቁልፍ ሚና ይኖረዋል” በማለት አክለዋል።
የጥቅምቱ ግጭት ዳራ
ያለፉት አስተዳደሮች ለብዙ ዓመታት ተቃውሞን በተደራጀ መልኩ ሲጨፈልቁ መቆየታቸውን ተከትሎ ከመጋቢት ወር 2011 ዓ.ም. ጀምሮ ስልጣን የያዙት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ የፖለቲካ እና ሲቪል ምሕዳሩን የማስፋት ዓላማ ያላቸው በርካታ የማሻሻያ እርምጃዎችን ወስደዋል። ይህም ከብዙ ዓመታት በኋላ ለመጀመሪያ ጊዜ ኢትዮጵያውያን በመሬት፣ በድንበር አከላለል፣ በሀገሪቱ ሀብቶች ተደራሽነት እና በማህበረሰባቸው ወይም ብሔረሰባቸው ላይ ተፈጽመዋል ብለው በሚያስቧቸው መድሎዎች ዙሪያ ያሏቸውን ለረጅም ጊዜ የቆዩ ቅሬታዎች ይበልጥ በነጻነት እንዲገልጹ እድሉን ሰጥቷቸዋል።
ይህ ይበልጥ ክፍት የሆነ የፖለቲካ ምህዳር የሀገሪቱ ፖለቲከኞች እና ምሁራን የብሔር ውጥረቶችን በማባባስ ያላቸውን ድጋፍ ለማጠናከር በተለያዩ ጊዜያት እንደፈለጉ ሲጠመዝዟቸው የቆዩ ብሔርተኛ አመለካከቶች እና ኃይሎች እንዲያንሰራሩም እንዲሁ ምቹ ሁኔታን የፈጠረ ሲሆን ይህም ያለመረጋጋት እና በማህበረሰቦች መካከል የሚፈጠር ግጭት እየጨመረ እንዲመጣ አስተዋጽኦ አድርጓል። ሀይማኖት እና ብሔር ኢትዮጵያ ውስጥ አብዛኛውን ጊዜ እርስ በርስ የተሳሰሩ በመሆናቸው ግጭቶቹ ማኖታዊ መልክ የያዙባቸው አንዳንድ አጋጣሚዎችም ነበሩ።
ባለፉት ሁለት ዓመታት ውስጥ የታዩት ያለመረጋጋቶች ከዚህም በተጨማሪ ከማሻሻዎች አዝጋሚነት ጋር ከተያያዙ ቅሬታዎች፣ በምዕራብ እና ደቡብ ኦሮሚያ በጸጥታ ኃይሎች ተፈጽመዋል የተባሉትን ጨምሮ ተፈጽመዋል ከሚባሉ አዳዲስ የመብት ጥሰቶች እንዲሁም ከቅርብ ጊዜ ወዲህ እየተባባሱ ለመጡት ማህበረሰባዊ ግጭቶች መንግስት ከሰጠው ምላሽ ወይም ምላሽ አልሰጠም ከሚለው አስተሳሰብ ጋር የተያያዙ ናቸው።
እነዚህ ክስተቶች የተፈጠሩት በፌዴራል፣ በክልል እና በአካባቢ ደረጃዎች ላይ ያሉ አስተዳደራዊ እና የጸጥታ ተቋማት በተዳከሙበት ሁኔታ ውስጥ ሲሆን ይህም በርካታ አካባቢዎች ላይ የጸጥታ ክፍተቶችን ከመፍጠሩም በላይ ግጭቶች በሚፈጠሩበት ወቅት ለመቆጣጠር የመንግስት ኃይሎች ዘግይተው ምላሽ እንዲሰጡ ወይም ከነጭራሹ እርምጃ እንዳይወስዱ ምክንያት ሊሆን ችሏል።
በተለያዩ ጊዜያት የተፈጠሩ ግጭቶች ግድያዎችን፣ የጅምላ እስሮችን፣ ከፍተኛ ቁጥር ያላቸው ሰዎች ከመኖሪያ ቀዬአቸው መፈናቀልን እና የንብረት ውድመትን አስከትለዋል። የሀገር ውስጥ መፈናቀል ክትትል ማዕከል (Internal Displacement Monitoring Center) የተሰኘው መንግስታዊ ያልሆነ የበጎ አድራጎት ድርጅት እ.ኤ.አ. እስከ ዲሴምበር ወር 2018 ዓ.ም. ድረስ በኢትዮጵያ ውስጥ 2.89 ሚሊዮን የተፈናቀለ ህዝብ መኖሩን ያረጋገጠ ሲሆን ይህም በዓለም ዙሪያ በአንድ ሀገር ውስጥ የተመዘገበው ትልቁ እንደ አዲስ የተፈናቀሉ ሰዎች ቁጥር ነው። ይህ ቁጥር እ.ኤ.አ. በ2018 ዓ.ም. የመጀመሪያዎቹ ጥቂት ወራት ውስጥ የተፈናቀሉ 1.4 ሚሊዮን ሰዎችን ጨምሮ ነው። ከዚህ በተጨማሪ እ.ኤ.አ. በ2019 ዓ.ም. የመጀመሪያው ግማሽ ዓመት ውስጥ 755,000 ሰዎች የተፈናቀሉ ሲሆን ከእነሱ ውስጥ 522,000 የተፈናቀሉት በግጭት ምክንያት ነበር።
ባለፉት ሁለት ዓመታት ውስጥ ከተፈጠሩት ያለመረጋጋቶች ውስት በጣም የብዙዎችን ህይወት የቀጠፈው የጥቅምቱ ግጭት ነበር። የተቃውሞ ሰልፎቹን የለኮሳቸው ገፊ ምክንያት የኦሮሞ አክቲቪስት እና የኦሮሚያ ሚዲያ ኔትወርክ (OMN) መስራች በሆነው በጃዋር መሀመድ ደህንነት ላይ መንግስት ስጋት ፈጥሯል የሚለው አስተሳሰብ ቢሆንም በርካታ ሰዎች ለሌሎች ቅሬታዎች የሰጡት ምላሽ ጭምርም ነበር። በዚህ ረገድ ጃዋር መሀመድ እና ደጋፊዎቹ ለሚያራምዱት አመለካከት እና ብሄርተኝነት ያላቸውን ተቃውሞ ለመግለጽ እና ብሔራችን ላይ ተፈጽሟል ብለው የሚያስቡትን ማኮሰስ ለመቃወም ጎዳናዎች ላይ በመውጣት ሰላማዊ ሰልፍ ያደረጉ ሌሎች ቡድኖችም ነበሩ።
እንደ ዐቢይ ሁሉ የኦሮሞ ብሄር ተወላጅ የሆነው ጃዋር ከ2007-2010 በቆየው እና በመጋቢት ወር 2010 ዓ.ም. ዐቢይን ስልጣን ላይ በማስቀመጥ በተጠናቀቀው የተቃውሞ እንቅስቃሴ ውስጥ ቁልፍ ሚናን ተጫውቷል። “ቄሮ” በመባል በሚታወቀው የኦሮሞ ወጣቶች እንቅስቃሴ ውስጥ ያሉትን ጨምሮ በኦሮሞ ማህበረሰብ ውስጥ ከፍተኛ ቁጥር ያላቸው ተከታዮች ነበሩት። በዩናይትድ ስቴትስ ውስጥ ለበርካታ ዓመታት በስደት ከኖረ በኋላ ጃዋር እ.ኤ.አ. በ2010 ዓ.ም. ዐቢይ ስልጣን ከያዘ በኋላ ወደ ኢትዮጵያ ተመልሷል። ከዚያም እ.ኤ.አ. 2019 ዓ.ም. ጃዋር የዐቢይን ፖሊሲዎች በግልጽ መቃወም ጀመረ።
ጥቅምት 11 ቀን ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ ለፓርላማ አባላት ባደረጉት ንግግር ያለመረጋጋትን ቀስቅሰዋል በማለት “ከውጭ ሀገር የመጡ የመገናኛ ብዙሃን ባለቤቶችን” በይፋ የወቀሱ ሲሆን ብዙ ሰዎች ይህን ወቀሳ በቅርቡ የአሜሪካ ዜግነቴን ሰርዤአለሁ ቢልም ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ ይህን ንግግር ባደረጉበት ወቅት ዜግነቱ አሜሪካዊ በነበረው በጃዋር ላይ እንደተሰነዘረ ትችት አድርገው ወስደውታል። በሚቀጥለው ቀንም መንግስት የመደበለትን ጥበቃ ባለስልጣን አካላት በእኩለ ሌሊት ሊያነሱበት እንደሞከሩ የጃዋር የደህንነት ቡድን አባላት ለጀዋር ነገሩት። ከዚያም ጃዋር ፌስቡክ ላይ ላሉት 1.75 ሚሊዮን ተከታዮቹ በመለጠፍ መልዕክት ያስተላለፈ ሲሆን ይህም ሰፊ ተቃውሞን ቀስቅሷል። ጃዋር የጥቅምቱን ግጭት ተከትሎ የኦሮሞ ተቃዋሚ ፓርቲዎች ጥምረትን የተቀላቀለ ሲሆን ይህም ማለት በነሀሴ ወር እንዲካሄድ በአሁኑ ወቅት ፕሮግራም በተያዘለት በመጪው ብሔራዊ ምርጫ ውስጥ የዐቢይ ተፎካካሪ ሆኖ ሊቀርብ ይችላል ማለት ነው።
ፖሊስ አምቦ ውስጥ ከመጠን ያለፈ እና ህልፈተ ህይወትን ያስከተለ ኃይል ስለመጠቀሙ
ከአዲስ አበባ በስተምዕራብ 100 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ የምትገኘው አምቦ ከተማ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ ወደ ስልጣን እንዲመጡ ምክንያት የሆነው ተቃውሞ የተቀጣጠለባት ከተማ ነበረች። ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ ወደ ስልጣን ከመጡ ከተወሰነ ጊዜ በኋላ ከተማዋን የጎበኙ ሲሆን ከዚያም የጥቅምቱ ግጭት ከተከሰተ ከአንድ ሳምንት በኋላ ወደዚያ በመሄድ ከአካባቢው ፖለቲከኞች ጋር ተገናኝተው ተወያይተዋል። ጠቅላይ ሚኒስትሩ ወደ ከተማው ባመሩበት ወቅትም በንዴት የተሞሉ ሰላማዊ ሰልፍ አድራጊዎች አቀባበል አድርገውላቸዋል።
ተቃውሞው የተጀመረው ጥቅምት 12 ቀን ጠዋት ላይ አብዛኞቻቸው የት/ቤት የደንብ ልብስ የለበሱ ተማሪዎች አውራ ጎዳና ላይ ተሰብስበው መንግስትን በመቃወም እና ጃዋርን በመደገፍ መፈክሮችን ማሰማት በጀመሩበት ወቅት ነበር። በኋላ ላይም ሌሎች ሰዎች የተቀላቀሏቸው ሲሆን ከእነዚህ ሰዎች ውስጥ አንዳንዶቹ አጠና የያዙ ነበሩ። ከሠዓት ላይ አንድ የፖሊስ አባል የሁለተኛ ደረጃ ት/ቤት ተማሪ የሆነ አንድ የተቃውሞ ሰልፍ አድራጊን በጥይት መምታቱን ተከትሎ ሠላማዊ የነበረው የተቃውሞ ሰልፍ መጥፎ አቅጣጫ ሊይዝ ችሏል። ከዚያም የተቃውሞ ሰልፍ አድራጊዎች ፖሊስ ላይ ድንጋይ መወርወር፣ መንገዶችን መዝጋት እና ጎማ ማቃጠል ጀመሩ። ያንን ተከትሎ ለ48 ሠዓታት በቆየው ግጭት ወቅት በርካታ የኦሮሚያ የጸጥታ ኃይል አባላት በተቃውሞ ሰልፍ አድራጊዎች ላይ አስለቃሽ ጭስ ለቀዋል እንዲሁም በጅምላ ጥይት ተኩሰዋል።
በተቃውሞ ሰልፎቹ ወቅት እንዲሁም ሰልፎቹን ተከትሎ አንድ አዛውንትን ጨምሮ ቢያንስ ስድስት ሰዎች ሁሉም በጥይት የተገደሉ መሆኑን እና አንድ የ13 ዓመት ታዳጊን ጨምሮ ቢያንስ 37 ሰዎች ጉዳት የደረሰባቸው መሆኑን የሰብአዊ መብት ጥበቃ አምቦ ውስጥ ከሚገኙ ተአማኒነት ያላቸው የህክምና ባለሞያዎች እና የዓይን እማኞች መረጃ ደርሶታል።
የመጀመሪያው ተቃውሞ ሰልፍ አድራጊ በጥይት ከተመታ በኋላ የተፈጠረውን ሁኔታ በአምቦ ዩኒቨርሲቲ አዋሮ ካምፓስ አካባቢ የነበሩ አንድ የዓይን እማኝ እንደሚከተለው ገልጸውታል፡-
ፖሊሱ ትከሻው ላይ ነበር በጥይት የመታው። አንድ ጊዜ ብቻ ነበር በጥይት የመታው – አልሞተም። ከዚያ [የተቃውሞ ሰልፍ አድራጊዎቹ] ስሜታዊ ሆነው ድንጋይ መወርወር ጀመሩ። ያኔ የጸጥታ ኃይሎቹ አስለቃሽ ጭስ መጠቀም ጀመሩ። … ሮጠን ሄደን ውሀ ማግኘት ነበረብን። ከዚያ በኋላ እኔ ታዳጊውን ደግፌ ወደ ሆስፒታል ይዤው ሄድኩኝ። ብዙም ሳይቆይ ሌሎች የተጎዱ ሰዎች [ወደ ሆስፒታሉ] መምጣት ጀመሩ።
ጥቅምት 12 ቀን የተደረገው የተቃውሞ ሰልፍ ላይ የነበረ አንድ ተማሪ ፖሊስ አንድ ሌላ ተማሪን በጥይት ሲመታ ተመልክቶ ነበር። በጥይት የተመታውም የ18 ዓመት ወጣት ጓደኛው ቢቂላ ሲርና ሲሆን የተመታውም የተቃውሞ ሰልፍ አድራጊዎቹ ፖሊስ ላይ ድንጋይ መወርወር ከጀመሩ በኋላ ነበር። “ጭንቅላቱ ላይ ነበር በጥይት የተመታው። ከነጭራሹ መናገር አቁሞ ስለነበር ወደ ሆስፒታል በፍጥነት ይዘነው ሄድን። የተመታበት ጥይት በጭንቅላቱ ውስጥ አልፎ ሌላ ሰው መትቷል።” ብሎ ነበር። ቢቂላ በደረሰበት ጉዳት ምክንያት ህይወቱ ሊያልፍ ችሏል።
ጥቅምት 13 የተቃውሞ ሰልፍ አድራጊዎች ዋናው ፖሊስ ጣቢያ ውጭ ላይ በመሰብሰብ የመጀመሪያውን የተቃውሞ ሰልፍ አድራጊ በጥይት የመታው የፖሊስ መኮንን በቁጥጥር ስር እንዲውል ጥያቄ በማቅረብ ላይ ነበሩ። የጸጥታ ሀይሎች በተሰበሰበው ህዝብ ላይ ተኩስ ሲከፍቱ የተመለከቱ የዓይን እማኝ የነበረውን ሁኔታ እንደሚከተለው ገልጸውታል፡-
የፖሊስ መኪና መጥቶ ሲቆም የተቃውሞ ሰልፍ አድራጊዎች ተሸከርካሪው ላይ ድንጋይ መወርወር ጀመሩ። ታዳጊውን ልጅ [የመጀመሪያውን የተቃውሞ ሰልፍ አድራጊ] በጥይት የመታውን ሰው ማየት ፈልገው ነበር። ... ያኔ ነበር ፖሊሶቹ ጥይት መተኮስ የጀመሩት። የተሰጠ ማስጠንቀቂያ አልነበረም። አንድ የፖሊስ መኮንን መተኮስ ሲጀምር ሁሉም መተኮስ ጀመሩ። ከዚያም የተቃውሞ ሰልፍ አድራጊዎቹ መሮጥ ጀመሩ፤ አብዛኞቻቸውም መሬት ላይ ወድቀው ነበር።
የተቃውሞ ሰልፍ አድራጊዎች ከዋናው መንገድ ወጥተው ወደ መኖሪያ አካባቢ ሲሸሹ የጸጥታ አባለላት ተከትለው አስለቃሽ ጭስ እና ጥይት ይተኩሱባቸው እንደነበር ሌላ ነዋሪ ገልጸዋል። በአካባቢው የነበሩ ሞሳ ሞሮዳ የተባሉ የ80 ዓመት አዛውንትን የጎረቤታቸው ቤት ውጭ ላይ ተቀምጠው እያለ ከተተኮሱት ጥይቶች ውስጥ በአንደኛው ጭንቅላታቸው ላይ ተመትተዋል። አንድ የዓይን እማኝ የሚከተለውን ብለዋል፡-
ከቤቴ ደጃፍ ላይ ስድስት የተቃውሞ ሰልፍ አድራጊዎች በጥይት ተመትተዋል። ተኩስ ስሰማ ምን ተፈጥሮ እንደሆነ ለማየት ወደ ውጭ ወጣሁ። እዚያ እያለሁ ሞሳ ሞሮዳን በጥይት መቷቸው። ከዚያም ፖሊሶቹ እኔን ሲያዩኝ ወደ እኔ መተኮስ ስለጀመሩ ሮጬ ተደበቅኩኝ።
አቶ ሞሳ በደረሰባቸው ጉዳት ምክንያት ህይወታቸው ሊያልፍ ችሏል።
በዶዶላ ስለነበረው ማህበረሰባዊ ግጭት
ዶዶላ በደቡብ ምስራቅ ኦሮሚያ የምትገኝ ከተማ ናት። እ.ኤ.አ. በ2007 ዓ.ም. የተደረገ አከራካሪ የህዝብ እና ቤት ቆጠራ እንደሚያሳየው ከሆነ ከተማዋ 20830 ነዋሪዎች ያሏት እና ከእነዚህም ውስጥ አብዛኛዎቹ የኦሮሞ ብሔር ተወላጆች ሲሆኑ ጥቂቶቹ ደግሞ የአማራ ብሔር ተወላጆች ናቸው።
ከጥቅምቱ ተቃውሞ አስቀድሞ በነበሩት ሳምንታት ውስጥ በተለያዩ ብሔረሰብ አባላት መካከል ያለው ውጥረት እየከረረ መምጣቱን የከተማው ነዋሪዎች ቢገልጹም በጥቅምት ወር የፈነዳው ግጭት ግን ታይቶ የማይታወቅ ነው ብለዋል።
የተቃውሞ ሰልፍ አድራጊዎች መጀመሪያ ላይ ወደ ጎዳና የወጡት መንግስት በጃዋር ላይ ፈጽሟል ያሉትን ነገር ለመቃወም ጥቅምት 12 ነበር። ከዚያም አጎራባች ሰፈሮች እና ወረዳዎች ውስጥ ያሉ ሰዎች መቀላቀል በመጀመራቸው ቀኑ እየገፋ ሲሄድ የተቃውሞ ሰልፍ አድራጊዎቹ ቁጥር እየጨመረ ሊመጣ ችሏል። የዚያን ቀን ጠዋት የሆነ ሰዓት ላይ የተወሰነ ቁጥር ያላቸው የተቃውሞ ሰልፍ አድራጊዎች በከተማዋ የሚገኝ የኦርቶዶክስ ቤተ-ክርስቲያን ወደሆነችው ወደ ገብረ ክርስቶስ አመሩ። የቤተ-ክርስቲያኑ ምዕመናንም የተቃውሞ ሰልፍ አድራጊዎቹ ወደ ቤተ-ክርስቲያኗ እንዳይገቡ ለመከላከል በሚመስል መልኩ አጠና ይዘው የገብረ ክርስቶስ ቤተ-ክርስቲያን በር ላይ ተሰብስበው ቆሙ። ይህም የተቃውሞ ሰልፍ አድራጊዎቹን የመለሳቸው ይመስል ነበር ምክንያቱም የዚያን ቀን ጠዋት ምንም ግጭት አልተፈጠረም ነበር፤ የተቃውሞ ሰልፍ አድራጊዎቹም ተመልሰው ወደ መሀል ከተማ ሄደው ነበር።
የዚያን ቀን ከሠዓት በኋላ ላይ ኪዳነ ምህረት ተብላ የምትጠራ ሌላ ቤተ-ክርስቲያን አካባቢ በተቃውሞ ሰልፍ አድራጊዎች እና በከተማው ነዋሪዎች መካከል እሰጥ አገባ ተጀመረ። ያንን ተከትሎ የዚያን ለት አመሻሹ ላይ ዶዶላ ሁለተኛ ደረጃ ት/ቤት አካባቢ በሚገኘው እና በብዛት የአማራ ብሔር ተወላጆች በሚኖሩበት ቀጠና 5 አካባቢ የተቃውሞ ሰልፍ አድራጊዎቹ ወደ ቤታቸው በመመለስ ላይ እያሉ በኦሮሞ የተቃውሞ ሰልፍ አድራጊዎች እና የአማራ ብሔር ተወላጅ በሆኑ ነዋሪዎች መካከል ከባድ ግጭት ተከሰተ። ከዚያም ግጭቱ ጥቅምት 13 ላይ ወደ ሌሎች መንደሮች ተስፋፍቶ የቀጠለ ሲሆን የተሰነዘሩት ጥቃቶች ግልጽ በሆነ መልኩ በተወሰነ ብሔር ተወላጆች እና የተወሰነ ሀይማኖት አባላት ናቸው ተብለው በሚታሰቡ ሰዎች ላይ ያነጣጠሩ ነበሩ።
ግድያዎች እና የአካል ጉዳቶች
የአይን እማኞች እና የተጎጂዎች ቤተሰቦች እንደገለጹት ከሆነ ነውጠኛ ቡድኖች ለሁለት ቀን በቆየው ጥቃት አንዲት ሴትን እና ሁለት ሽማግሌዎችን ጨምሮ በከተማዋ የሚኖሩ የተለያዩ ብሔረሰቦች አባላት እና የተለያዩ ሀይማኖት ተከታዮች የሆኑ ቢያንስ 10 ሠዎችን ገድለዋል። የጥቃት ሰለባዎችን በጥይት በመምታት፣ የተለያዩ የሰውነት ክፍሎቻቸውን በመቆራረጥ ወይም ደብድቦ በመግደል ጥቃቶች ተፈጽመዋል። ህጻናትን ጨምሮ ቢያንስ ሌሎች 60 ሰዎች ጉዳት የደረሰባቸው ሲሆን ከእነሱም ውስጥ አንድ የ12 ዓመት ህጻን ይገኝበታል። ጉዳት የደረሰባቸው እና የተገደሉ ሰዎች ትክክለኛው ቁጥር እዚህ ጋር ከተገለጸው በላይ ሊሆን ይችላል።
የተወሰነ ቁጥር ያላቸው ኦሮሞ የተቃውሞ ሰልፍ አድራጊዎች በቀጠና 5 አልፈው ወደ ቤታቸው በመመለስ ላይ እያሉ የአማራ ብሔር ተወላጅ የሆኑ ወጣቶች ድንጋይ እና አጠና እንደወረወሩባቸው የዓይን እማኞች ገልጸዋል። በቦታው የነበሩ አንድ አዛውንት እንዲህ ብለዋል፡-
የተወሰንን አዋቂዎች ጩኸት ሰምተን ለማስታረቅ እና ሁኔታውን በሽምግልና ለመፍታት ወደ አካባቢው ሮጠን ሄድን። ነገር ግን አልተሳካልንም። ከዚያም ፈንጅ ስለተወረወረ ሸሽተን ሮጥን። ብዙ ሰዎች ተጎድተው ነበር። እስከ አመሻሽ ድረስ የተኩስ ድምጽ ይሰማኝ ነበር።
በጥይት የተመቱ ወደ 20 የሚጠጉ ሰዎችን ጨምሮ በአብዛኛው የኦሮሞ ማህበረሰብ አባል የሆኑ ጉዳት የደረሰባቸው የተቃውሞ ሰልፍ አድራጊዎች ጥቅምት 12 ቀን ከሠዓት በኋላ ቆይተው ወደ ሆስፒታሉ መግባት እንደጀመሩ በዶዶላ ጠቅላላ ሆስፒታል የሚሠሩ ሁለት የጤና ባለሞያዎች አረጋግጠዋል። በጩቤ የተወጉ ወይም በፈንጅ ጉዳት የደረሰባቸው ሌሎች ሰዎችም ነበሩ። ጥቅምት 12 ቀን በጥይት ተመትተው ወደ ሆስፒታሉ ከመጡት ሰዎች ውስጥ አራቱ በደረሰባቸው ጉዳት ምክንያት ህይወታቸው አልፏል።
ሌሎች አራት ነዋሪዎች ጥቅምት 13 ቀን ጠቅላላ ሆስፒታሉ ውስጥ በተፈጸመባቸው ጥቃት ህይወታቸው ማለፉን የዓይን እማኞች ገልጸዋል። አንድ የዓይን እማኝ የሚከተለውን ብለዋል፡-
ጉዳት የደረሰባቸው ሦስት ሰዎች በአምቡላንስ ተጭነው ወደ ሆስፒታሉ የመጡ ሲሆን ወደ ድንገተኛ ህክምና ክፍል ተወስደው ነበር። አንድ ታዳጊ፣ አባቱ እና አንድ አዛውንት ነበሩ። … በቀደመው ቀን በነበረው ግጭት ጉዳት ደርሶባቸው የነበሩ ኦሮሞ ታካሚዎች ሦስቱ ሰዎች አማራ መሆናቸውን ወዲያውኑ ለይተው እንዲህ አሉ፡- “እነዚህ አማራዎች ናቸው፤ እንዳታክሟቸው”።
የሆስፒታሉ ሠራተኞች በኋላ ላይ ሦስቱ ሰዎች ጭንቅላታቸው ላይ በደረሰባቸው ከፍተኛ ጉዳት ህይወታቸው አልፎ አገኟቸው። በተጨማሪም አንዲት ሴት ካፊቴሪያው ውስጥ ድብደባ እንደተፈጸመባት ገልጸዋል። በደረሰባት ድብደባ ጭንቅላቷ እና ፊቷ ላይ ክፉኛ ተጎድታ ነበር። ከዶዶላ 97 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ የምትገኘው ሀዋሳ ከተማ ውስጥ ወዳለ ሌላ ሆስፒታል ተወስዳ በዚያ ህይወቷ ሊያልፍ ችሏል።
አንድ ሀኪም “ሆስፒታሉ ውስጥ የነበረው ሁኔታ ከእኛ ቁጥጥር ውጭ ነበር። ለአካባቢው የጸጥታ ሀይሎች ጥሪ ብናስተላልፍም በጊዜ አልደረሱልንም” ብለዋል።
በሆስፒታሉ ውስጥ ህይወታቸው ካለፈው ስምንት ሰዎች በተጨማሪ ቢያንስ ሁለት አዛውንት በቤታቸው ውስጥ እያሉ በነውጠኛ ቡድኖች መገደላቸውን ነዋሪዎች ገልጸዋል። በቤታቸው ላይ ጥቃት በሚፈጸምበት ወቅት አዛውንት ዘመዳቸውን ጥለው ወደ ኪዳነ ምህረት ቤተ-ክርስቲያን ለመሸሽ መገደዳቸውን የገለጹ አንድ ግለሰብም ነበሩ። በኋላ ላይም ዘመዳቸው ሰውነታቸው ተቆራርጦ መገደላቸውን ለማወቅ ችለዋል፡-
[ነውጠኛ ቡድኖች] ወስደው ሆዳቸውን፣ እግራቸውን እና እጃቸውን ቆራረጧቸው። ይህ ሲፈጸም … እኔ እዚያ አልነበርኩም … [ወደ ቤተ-ክርስቲያኑ] ልንወስዳቸው አልቻልንም ነበር፤ ሁኔታው የሚፈቅድ አልነበረም። የፌዴራል መንግስት ኃይሎች በኋላ ላይ አስከሬናቸውን ወደ ቤተ-ክርስቲያኑ አመጡት እና ጥቅምት 14 ቀን ቀበርናቸው።
በንብረት ላይ የደረሰ ውድመት
ድንጋይ፣ አጠና እና የግብርና መሳሪያዎች የያዙ ነውጠኛ ቡድኖች ንብረታቸውን እንደዘረፉ እና እንዳቃጠሉባቸው ሦስት ነዋሪዎች ገልጸዋል። የሰብአዊ መብት ጥበቃ ከጳጉሜ 5 እስከ ጥቅምት 21 ድረስ ባለው ጊዜ ውስጥ ዶዶላ ላይ የተነሳ የሳተላይት ምስልን የገመገመ ሲሆን ይህም ቃለ መጠይቅ የተደረገላቸው ሰዎች በገለጿቸው አካባቢዎች ውስጥ ከ30 እስከ 40 የሚደርሱ ህንጻዎች ጉዳት የደረሰባቸው መሆኑን አረጋግጧል። ከቃጠሎ አደጋ ጋር ተመሳሳይ የሆነው ይህ ጉዳት የአማራ ብሔር ተወላጆች በብዛት የሚኖሩበት ሰፈር በሆነው ቀጠና 5 ውስጥ በሚገኘው ዶዶላ ሁለተኛ ደረጃ ት/ቤት እና ዶዶላ ጋባ ካሚሳ አካባቢ እንዲሁም ገብረ ክርስቶስ ቤተ-ክርስቲያን የሚገኝበት አካባቢ ላይ ያነጣጠረ ሲሆን ጉዳት በደረሰባቸው አብዛኛዎቹ ህንጻዎች ዙሪያ በቃጠሎ የወደመ የፍርስራሽ ክምር መኖሩን ምስሉ ያሳያል።
ጥቅምት 12 ቀን ከሠዓት በኋላ መጠለያ ፍለጋ ወደ ኪዳነ ምህረት ቤተ-ክርስቲያን የሄዱ አንድ ነዋሪ ነውጠኞቹ የቤተ-ክርስቲያኗ በር ላይ ሲደርሱ ስለነበረውን ሁኔታ ያዩትን እንደሚከተለው ገልጸውታል፡-
በከተማው የሚኖሩ አዛውንቶች እና የኦሮሚያ ልዩ ኃይል ስላስቆሟቸው መግባት አልቻሉም ነበር። ስለዚህ [ነውጠኞቹ] ቤተ-ክርስቲያኗን ከበው ድንጋይ መወርወር ጀመሩ። …እኛም ድንጋዩን ሰበሰብን እና መልሰን መወርወር ጀመርን። ቤተ-ክርስቲያኗ ውስጥ ብዙ ሰዎች ጉዳት ደርሶባቸው ነበር።
የክልሉ የፖሊስ ኃይል ሰዎች እንዳይገቡ እና እንዳይወጡ ለመከላከል ኪዳነ ምህረት ቤተ-ክርሰቲያን አጠገብ አስለቃሽ ጭስ እንደተኮሱ እና ይህም በሰዎች ላይ ጉዳት እንዳደረሰ እና መደናገጥን እንደፈጠረ ሌላ የዓይን እማኝ ገልጸዋል። “አንዳንዶቻችን ቤተ-ክርሰቲያኗ ውስጥ በሩ አጠገብ ቆመን ነበር። ሰዎች [በአስለቃሽ ጭሱ የተነሳ] በማስመለስ ላይ ነበሩ፣ እኔንም ዓይኔን ጎድቶት ነበር እንዲሁም መተንፈስ አቅቶኝ ነበር” ብለዋል።
ጥቅምት 12 ቀን በዶዶላ ሁለተኛ ደረጃ ት/ቤት አቅራቢያ በሚገኝ ሱቃቸው ላይ ጥቃት ተፈጽሞባቸው የነበረ አንድ ነጋዴ እንዲህ ብለዋል፡- “ቄሮዎች ወደ ሱቄ መጡ፤ ቁጥራቸው በጣም ብዙ ነበረ። ሱቄን እና ቤቴን ዘረፉ። ድንጋይ፣ ጩቤ፣ ገጀራ እና አጠና ይዘው ነበር።”
ጥቅምት 12 ቀን ቤቷ ጥቃት ተፈጽሞበት የነበረች አንዲት ሴትም እንዲህ ብላለች፡-
[ነውጠኞቹ] ወደ እያንዳንዱ መኝታ ክፍል ገቡ፤ አልጋዎቹን ስባበሯቸው፤ የሻይ እና የቡና ማፍያ ማሽኖቹን ሰበሯቸው፤ ፍሪጁንም ውጭ አውጥተው ወረወሩት። ስንት እንደነበሩ እርግጠኛ አይደለሁም፤ መዶሻ እና ድንጋይ ይዘው ቤቱን ከበቡት። ውጭ ላይ የነበረውን ንብረት በሙሉ አቃጠሉት።
ይህም ከ30 ደቂቃ እስከ አንድ ሠዓት ለሚያክል ጊዜ ቀጠለ።… ከዚያ [የኦሮሚያ ልዩ ፖሊስ እና ዶዶላ ፖሊስ] መጡ። ከዚያም ጥይት [ወደ ላይ] በመተኮስ አመጸኞቹን በተኗቸው።
ጥቃቱ ከተፈጸመ በኋላ ወዲያውኑ ቢያንስ 3,000 ሰዎች ከተማዋ ውስጥ በሚገኙት ሁለት ቤተ-ክርስቲያናት ውስጥ ተጠልለው እንደነበር ነዋሪዎች እና የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ገልጸዋል። በተጨማሪም ጉዳት በደረሰባቸው ህንጻዎች አቅራቢያ በምትገኘው የዶዶላ ደቡብ ምዕራባዊ ክፍል ከጥቅምት 14 እና 15 ጀምሮ ጊዜያዊ መጠለያዎች መሰራታቸውን ከሳተላይት የተገኙ ምስሎች ያሳያሉ።
አባ ገዳዎች (የኦሮሞ ሽማግሌዎች እና ባህላዊ መሪዎች) እርቅ ለመፍጠር ባደረጉት ጥረት አንዳንድ ነዋሪዎች ወደ ቤታቸው ለመመለስ ችለዋል። እስከ መጋቢት ወር መጀመሪያ ባለው ጊዜ ውስጥ ተጨማሪ ግጭቶች ይቀሰቀሳሉ በሚል ፍርሀት የተነሳ በርካታ ተፈናቅለው የነበሩ ሰዎች ዶዶላን ለቀው ሄደዋል። በጥቃቶቹ የተነሳ የተፈናቀሉ አንድ ግለሰብ የኑሮው ሁኔታ በጣም አስቸጋሪ እንደሆነ እንዲህ ሲሉ ገልጸዋል፡- “መንግዳችን ተዘግቷል። ሥራ ፈትተን ነው ተቀምጠን ያለነው። ክርስቲያኖች ወደ ሥራ ለመመለስ ፈርተው ያሉበት ሁኔታ ነው ያለው።”
የመንግስት ምላሽ
ጥቅምት 20 ቀን አንድ የመንግስት ቃል አቀባይ ከደርዘን በላይ በሆኑ ከተሞች ውስጥ በጥቅምት ወር ከተቀሰቀሰው ግጭት ጋር በተያያዘ ከ400 በላይ ሠዎች በቁጥጥር ስር መዋላቸውን ገልጸዋል።
የአምቦ እንዲሁም የዶዶላ ነዋሪ የሆኑ ሰዎች የክልሉ የመንግስት ባለስልጣናት ምርመራ የጀመሩ መሆኑን ገልጸዋል። አምቦ ውስጥ የምዕራብ ሸዋ ዞን ባለስልጣን አካላት በጉዳዩ ላይ ምርመራ የሚያከናውን ኮሚቴ ያቋቋሙ መሆኑ የተገለጸ ሲሆን የኦሮሚያ ፖሊስ ኮሚሽንም እንዲሁ የራሱን ምርመራ ማከናወን ጀምሯል። በፖሊስ የተፈጸመውን ጥቃት የተመለከቱ አንድ ቁልፍ ምስክር በጥቃቱ ውስጥ የተሳተፉ የጸጥታ ሀይል አባላትን እንዲጠቁሙ ከዞኑ የፖሊስ አባላት ጥያቄ እንደቀረበላቸው ለስብአዊ መብት ጥበቃ ተናግረዋል።
የካቲት 13 ቀን ለሰብአዊ መብት ጥበቃ በተጻፈ ደብዳቤ የፌዴራል ጠቅላይ አቃቤ ሕግ ጽ/ቤት አምቦ ላይ ምርመራ በሂደት ላይ ቢሆንም “በዜጎች እንዲሁም በጸጥታ ኃይሎች በኩል ህልፈተ ህይወቶች የተመዘገቡ” መሆኑን የተገኙት የመጀመሪያ ደረጃ መረጃዎች እንደሚያሳዩ ገልጿል።
ዶዶላ ውስጥ የዞኑ ባለስልጣን አካላት የምርመራ ቡድን ወደ ከተማዋ የላኩ መሆኑን አንዳንድ ነዋሪዎች ገልጸዋል። በተጨማሪም ዶዶላ ውስጥ በክፍት ችሎት ክስ የመስማት ሂደት የተጀመረ መሆኑን የጠቅላይ አቃቤ ሕግ ጽ/ቤት ገልጿል። ነገር ግን በዞኑ ምርመራ ውስጥ ትብብር ያደረጉ አራት ቁልፍ ምስክሮች ከባለስልጣን አካላቱ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ የደረሳቸው ምንም መረጃ እንደሌለ እና እስከ የካቲት መጨረሻ ድረስ በክፍት ችሎት ክስ የመስማት ሂደት ስለመጀመሩ የሚያውቁት ነገር እንደሌለ ገልጸዋል።
ለኢትዮጵያ መንግስት የቀረቡ ምክረ-ሀሳቦች
ሕግ የማስፈጸም ግዴታ ያለባቸው የኢትዮጵያ ፌዴራል እና የክልል የጸጥታ ሀይሎች የሕግ አስፈጻሚ አካላትን የሀይል እና የመሳሪያ አጠቃቀም በተመለከተ የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ያወጣቸውን መሠረታዊ መርሆዎች በጥብቅ ማክበር ይኖርባቸዋል። በእነዚህ መርሆዎች መሰረት የጸጥታ ሀይሎች ሀይል ወደ መጠቀም ከመሄዳቸው በፊት ከሀይል እርምጃ ውጭ ሌሎች ዘዴዎችን ተግባራዊ ማድረግ አለባቸው። ህግ አስፈጻሚ አካላት ለህልፈተ ህይወት ሊያበቃ የሚችል ሀይል መጠቀም ያለባቸው ህይወት ሊያጠፋ ወይም አካላዊ ጉዳት ሊያደርስ የሚችል የቀረበ አደጋን ለመከላከል ፍጹም አስፈላጊ ሲሆን ብቻ ነው። ነውጠኛ የተቃውሞ ሰሰልፍን ለመበተን ሀይል መጠቀም የግድ አስፈላጊ ከሆነ የጸጥታ ሀይሎች የሚጠቀሙት ሀይል ሁኔታውን ለመቆጣጠር በሚያስፈልገው መጠን ብቻ ዝቅተኛ መሆን አለበት። በተጨማሪም የጸጥታ ሀይሎች ጉዳት የደረሰባቸው ሰዎች በተቻለ መጠን በቶሎ የህክምና እርዳታ እንዲያገኙ ማድረግ አለባቸው።
የኢትዮጵያ መንግስት፡-
- የጸጥታ ሀይሎች ተጠቀሙ በተባለው ከመጠን ያለፈ ሀይል እና ማህበረሰባዊ ጥቃት በፈጸሙ ሰዎች በተፈጸመው የጭካኔ ድርጊት ላይ ተአማኒነት ያለው፣ ገለልተኛ እና ግልጽ ምርመራ እንዲካሄድ ድጋፍ ማድረግ አለበት። በዚህ ረገድ የሚደረገው ምርመራ ህይወታቸው ያለፈ እና የአካል ጉዳት የደረሰባቸው ሰዎችን፣ ህልፈተ ህይወትን ወይም የአካል ጉዳትን ባስከተለው እያንዳንዱ ክስተት ዙሪያ ያሉትን ሁኔታዎች እና የመንግስት የጸጥታ ሀይሎች በሰብአዊ መብት ጥሰቶች ውስጥ ምን ያህል ተሳትፎ አድርገዋል የሚሉትን ጉዳዮች በተሟላ መልኩ ያካተተ ሊሆን ይገባል።
- በተቃውሞ ሰልፍ አድራጊዎች ላይ ከመጠን ያለፈ ሀይል በተጠቀሙ ሁሉም የጸጥታ ኃይሎች ላይ ማዕረጋቸው ወይም ኃላፊነታቸው ምንም ይሁን ምን የስነ-ምግባር እርምጃ እንዲወሰድ ወይም ለፍርድ እንዲቀርቡ ማድረግ አለበት።
- በማንኛውም ሁኔታ ሀይል መጠቀም ያለባቸው ተጨባጭ እና የቀረበ ስጋትን ለመከላከል የግድ አስፈላጊ እና አግባብ ከሆነ ብቻ እንደሆነ እና ከመጠን ያለፈ ሀይል መጠቀም ቅጣትን እንደሚያስከትል ህግ አስፈጻሚ አካላት እና የጸጥታ ኤጀንሲዎች ለሰራተኞቻቸው ግልጽ ትእዛዝ እንዲያስተላልፉ መመሪያ መስጠት አለበት። መሳሪያ የሚይዙ የሕግ አስፈጻሚ አባላት መሳሪያ መያዝ ሊፈቀድላቸው የሚገባው በአጠቃቀሙ ዙሪያ ልዩ ስልጠና ወስደው ካጠናቀቁ በኋላ ብቻ ነው። የሀይል እና የመሳሪያ አጠቃቀማቸውን ውስን ለማድረግ ሲባል ለህግ አስፈጻሚ አባላት የሚሰጡ ስልጠናዎች ሀይልን እና መሳሪያን ከመጠቀም ውጭ ላሉ አማራጮች ልዩ ትኩረት መስጠት አለባቸው።
- ያለመረጋጋቶች በሚኖሩበት ወቅት ሆስፒታሎች እና ሌሎች የህክምና አገልግሎት መስጫዎች በቂ የጸጥታ ሀይል የሚመደብላቸው መሆኑን ማረጋገጥ አለበት።
- ማህበረሰባዊ ጥቃት የደረሰባቸው ተጎጂዎች ካሳ እንዲያገኙ የሚያስችል ፕሮግራም መዘርጋት የሚለውን ጉዳይ ሊያስብበት ይገባል እንዲሁም ካሳው ጊዜውን የጠበቀ፣ በቂ እና ግልጽ በሆነ መልኩ መሰጠቱን ማረጋገጥ አለበት።
- በተጎጂዎች እና በቤተሰቦቻቸው ላይ ለሚደርሱ አካላዊ እና አእምሮአዊ ጉዳቶች የጤና እንክብካቤ እና ድጋፍ መስጠት አለበት።
- ማህበረሰባዊ ጥቃቶች በደረሱባቸው አካባቢዎች የማህበረሰብ ስብሰባዎችን ማድረግን ጨምሮ የወንጀል ተጎጂዎች የፍርድ ሂደቶችን የጊዜ ሰሌዳ እና አፈጻጸም እንዲሁም በጉዳያቸው ላይ የተሰጠውን ውሳኔ በተመለከተ መረጃ እንዲያገኙ ማድረግ አለበት።
- መድሎን እና ጥቃትን በማስቀረት አስፈላጊነት ላይ ባተኮሩ መጠነ ሰፊ ህዝባዊ የትምህርት ዘመቻዎች አማካኝነት ብሔረሰቦች እና ሀይማኖታዊ ማህበረሰቦች የሚሰማቸውን ፍርሀት ለማርገብ የሚያስችሉ ትርጉም ያላቸው እርምጃዎችን መውሰድ አለበት።