Skip to main content

ኢትዮጵያ: ለዓመታት በሶማሌ ክልል ዉስጥ የተፈጸሙት ሰቆቃዎች ላይ ጥልቅ ምርመራ ያስፈልጋል፡፡

ተፈጸሙ ወንጀሎች ካሳ እና ተጠያቂነት ማስፈን ያስፈልጋል

ከሶማሌ ክልል ጎዴ ዞን ኢሜይ ከተማ የመጣችው ስደተኛ ሴት በኬንያ ደዳብ የስደተኞች ካምፕ ዉጪ ቆማ። ልጆችዋን ይዛ የተሰደደችው በ2007 እኤአ  በመንግስት የጸጥታ ሀይሎች ባሏ ከተገደለ በኋላ ነበር።   © Evelyn Hockstein

 

የኢትዮጵያ መንግስት በኢትዮጵያው ሶማሌ ክልል ዉስጥ ለዓመታት ሲፈጸሙ በቆዩት የመብት ጥሰቶች እና ህገወጥነቶች ላይ ጥልቅ እና ገለልተኛ ምርመራ ለማካሄድ ቁርጠኛ መሆን አለበት ሲል ሂውማን ራይትስ ዎች ዛሬ ባወጣው መግለጫ ይጠይቃል። የዚህ ምርመራ ሂደት የቀድሞ የክልሉ ፕሬዝዳንት አብዲ መሀመድ ኦመር እና አሁንም የክልሉ ልዩ ፖሊስ ሀላፊ የሆነዉን ኣብድራህማን ኣብዱላሂ ቡረሌን ጨምሮ ከፍተኛ የመንግስት ባለስልጣናት የነበራቸዉን ሚና በጥልቀት የሚመረምር መሆን አለበት።

ነሓሴ 6, 2018 አስከፊው የሶማሌ ልዩ ፖሊስ እና ለአብዲ ኢሌይ ታማኝ የሆኑት ወጣቶች በጅግጅጋ ነዋሪዎች እና ንብረታቸው ላይ ጥቃት መፈጸማቸውን ተከትሎ የክልሉ ፕሬዘዳንት አብዲ ኢሌይ ስልጣን ለቋል። “የኢትዮጵያ መንግስት ከቀድሞ የመብት ጥሰት ታሪኩ ለመላቀቅ ላለፉት አስርት ዓመታት በሶማሌ ክልል ስፈጸሙ በነበሩት አሰቃቂ የመብት ጥሰቶች ላይ ፍትህን ሊያሰፍን ይገባል’’ ብለዋል የምስራቅ አፍሪካ እና የአፍሪካ ቀንድ የሂውማን ራይትስ ዎች ተመራማሪ የሆኑት ማሪያ በርኔት። አክለዉም “የጠቅላይ ሚንስትር አብይ አህመድ የለውጥ አጀንዳ አሰቃቂ ሰብአዊ መብት ጥሰት የፈጸሙት ግለሰቦች በስልጣናቸው ተከልለው ከተጠያቂነት እንዳያመልጡ ማረጋገጥ አለበት” ብለዋል።

የሶማሌ ክልል በኢትዮጵያ እና ሶማሊያ ድንበር ላይ የሚገኝ ስትራቴጅካዊ ክልል ነው። ይሄ ክልል ላለፉት አስርት ዓመታት በልዩ ፖሊስ እና በአገር መከላከያ ሰራዊት ሰፋፊ የመብት ጥሰቶች ሲፈጽሙበት የነበረ ክልል ነው። የክልሉ የሚደረጉ ክንውኖች ላይ ያለው መረጃ ትኩረት ከ2007 ጀምሮ በእጅጉ የተወሰነ ነው። ጋዜጠኞች፣ የእርዳታ ድርጅቶች፣ የሰብአዊ መብት ተቋማት እና ሌሎች ገለልተኛ የምርመራ ቡድኖች ክልሉ ዉስጥ አንዳይንቀሳቀሱ ተገድበዋል።

በአማጺው የኦጋዴን ነጻ አውጪ ግንባር (ኦብነግ) እና የኢትዮጵያ መከላከያ ሰራዊት መካከል የነበረው ጦርነት በ2007 አም ከተባባሰበት ግዜ ጀምሮ የጅምላ በደሎች በሰፊው ሲፈጸሙ ነበር። የኢትዮጵያ ባለስልጣናት በጊዜው የክልልሉ የጸጥታ ሀላፊ ለነበረው እና በኃላ ላይ ለስምንት ዓመታት የክልሉ ፕሬዝዳንት ሆኖ ለቆየው ለአብዲ ኢሌይ ሪፖርት የሚያደርገዉን ልዩ ፖሊስ የፈጠሩት ኦብነግን ለመመከት ነበር።

ሂውማን ራይትስ ዎች 2008 ባወጣው ሪፓርት የኢትዮጵያ የጸጥታ አካላት እና አማጺ ቡድኖች ከ2007 አጋማሽ እስከ 2008 መጀመሪያ በሶማሌ ክልል ህዝብ ላይ የጦር ወንጀል እንደፈጸሙ ዘግቦ ነበር። የኢትዮጵያ መከላከያ ሰራዊት የአስገድዶ መድፈሮች፣ ማሰቃየቶች፣ በግድ ከቀዬ መፈናቀሎችን ያካተተ ሰብአዊ ወንጀሎችን ፈጽሞ እንደነበር ሪፓርቱ ያሳያል። የኢትዮጵያ መከላከያ ሰራዊት አባላት መሉ የገጠር ህብረተሰብን ከቄያቸው በጉልበት በማፈናቀል፣ ብዙ ቀበሌዎችን አውድመው፣ ህብረተሰቡን ለማሸበር ኣስበው 150 ሰዎች ላይ ህዝብ ፊት የጅምላ ግድያ እንደፈጸሙ ሂውማን ራይትስ ዎች ሪፓርት ያሳያል። የጸጥታ አካላት በመቶዎች የሚቆጠሩ ግለሰቦችን በዘፈቀደ አስረው የመድፈር እና ብዙ ጾታዊ ጥቃቶችን ሲፈጽሙ እንደነበርም ተገልጧል። በዚህ ጊዜ በተፈጸሙት ወንጀሎች ላይ ገለልተኛ ምርመራ እንዲደረግ ሂውማን ራይትስ ዎች በተደጋጋሚ ሲጠይቅ እንደነበር ይታወሳል።

በ2008 የኢትዮጵያ የዉጭ ጉዳይ ሚንስትር ሂውማን ራይትስ ዎችን ጥያቄ መሰረት በማድረግ ምርመራ ጀምሮ ነበር። ይሁን እንጅ ምርመራው በዋናነት የመንግስትን ሚና ለመሸፈን በማለሙ ታአማኒነት እና ገለልተኛነት የጎደለው ነበር። የኢትዮጵያ መከላከያ ሰራዊት ሀላፊዎች ዜጎች ላይ ሲፈጸሙ በነበሩ ጥቃቶችን በማዘዝም ይሁን በቀጥታ በመሳተፍ የነበራቸው ሚና እና ሀላፊነትን ያካተተ አዲስ ምርመራ ያስፈልጋል። በተጨማሪም ይሄ ወንጀል መፈጸሙን የሚያዉቁ እና ምንም ማስተካከያ እርምጃ ያልወሰዱ እንዲሁም ማወቅ የነበረባቸው የሰራዊቱ እና የመንግስት ከፍተኛ ሀላፊዎች ሃላፊነትን ባለመወጣት ተጠያቂ መሆን ይገባቸዋል።

ከቅርብ ዓመታት ወዲህ የመከላከያ ሰራዊት ቀጥተኛ ተሳታፊነቱን የቀነሰ ቢሆንም በአብዲ ኢሌይ ቁጥጥር ስር የነበረው ልዩ ፖሊስ በኦብነግ ደጋፊ ናቸው ተብለው በሚጠረጠሩ ሰዎች ላይ ከፍተኛ በደል ሲፈጽም ነበር። ይሄ ልዩ ፖሊስ ባለፈው አስር አመት የዘፈቀደ ግድያዎችን፣ አስገድዶ መድፈሮችን በክልሉ ህብረተሰብ እና ሌሎች ህዝቦች ላይ ሲፈጽም ቆይቷል። ከታህሳስ 2016 አም ጀምሮ ደግሞ ከሶማሌ ክልልም አልፎ በኦሮሚያ ክልል ውስጥ በመቶዎች የሚቆጠሩ የሰዎች ህይወትን እየቀጠፈ እና ሰፋፊ መፈናቀሎች የደረገ ሲሆን በሶማሌ ዉስጥም ጥቃት እና ረብሻ ሲፈጽም እንደነበረ መረጃዎች ያሳያሉ።

ሂውማን ራይትስ ዎች ሓምሌ 2018 ባወጣው ሪፖርት በሶማሌ ክልል ማዕከላዊ እስር ቤት በሆነው እና የኦጋዴን እስር ቤት በመባል በሚታወቀው በሶማሌ ክልል ልዩ ፖሊስ ቁጥጥር ስር ባለው እስር ቤት የሚፈጸሙትን ዘግናኝ ማሰቃየቶች በሰነድ አዘጋጅቶ ይፋ አድርጓል። የቀድሞ እስረኞች በእስር ቤቱ ሲፈጸሙ የነበሩትን ድብደባዎች እና በደሎች እንዲሁም በቂ ያልሆነ የጤና አገልግሎት፣ የቤተሰብ ጉብኝት እና የጠበቃ አገልግሎት ይባስ ብሎም በቂ ያልሆነ ምግብ አለመገኘቱን መስክረዋል። እስረኞች ላይ ሲፈጸሙ የነበሩትን ወንጀሎች በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ የተሳተፉት ሀላፊዎች ያለምንም ስልጣን ከለላ ሊመረመሩ እና በማስረጃ የተረጋገጠባቸው ላይ የወንጀል ክስ መመስረት አለበት ብሏል ሂውማን ራይትስ ዎች። በምርመራው ዉስጥ የቀድሞ የሶማሌ ክልል ፕሬዝዳንት አብዲ ኢሌይ እና ኣብድላሂ ቡራሌ ( በተለምዶው ስሙ አብዱላሂ ላባጎሌ) ተሳትፎ በጥልቀት መታየትም ይኖርበታል።

የኢትዮጵያ መንግስት፣ በአለማቀፉ ህግ መሰረት የጦር ወንጀል የፈጸሙ የመከላከያ አባላትን እና ግለሰቦችን መርምሮ ለህግ የማቅረብ ግዴታ አለበት። የሰብአዊ ወንጀል እና በጣም ከባድ የሰብአዊ መብት ጥሰት ለፈጸሙ ግለሰቦች ይቅርታ ሊታለፉ አይገባም።

በክልሉ የሚፈጸሙትን የመብት ጥሰቶች ያጋለጡ ግለሰቦች ላይ የክልሉ መንግስት የበቀል እርምጃ ሲወሰድባቸው እንደነበረም የሚታወስ ነው ። ለምሳሌ በ2016 በአዉስትራሊያ ሜልቦርን በተደረገው ስልፍ ላይ የተሳታፉ ሰልፈኞችን ለመበቀል ሲባል ቤተሰቦቻቸዉን ኣስረው ለወራት እንዳቆዪአቸው ሂውማን ራይትስ ወች በወቅቱ ዘግቧል፡፡

በሶማሌ ክልል ዉስጥ ላለፉት ዓስርት ዓመታት ሲፈጸሙ በነበሩት ወንጀሎች እና በደሎች ላይ ጥልቅ እና ገለልተኛ ምርመራ ማድረግ የጠቅላይ ሚኒስተር አብይ አህመድ የሪፎርም አካል መሆን አለበት ብሏል ሂውማን ራይትስ ዎች። በኢትዮጵያ እየተካሄደ ያለውን ሪፎርም የሚደግፉ ወዳጅ ሀገሮች በዚህ ዙሪያ የቴክኒክ ድጋፍ ማድረግ ይጠበቅባቸዋል። ምርመራው ተአማኒነት የተረጋገጠ እንዲሆን የምርመራው ዉጤት አለማቀፍ ባለሞያዎችን ያሳተፈና እና መስፈርት ያሟላ ሆኖ ውጤቱም በግልጽ ይፋ መደረግ ይኖርበታል።

“ለጊዜያዊ የፖለቲካ ፍጆታ ሲባል የፌዴራል መንግስቱ እንደዚህ አይነት አሰቃቂ ወንጀሎችን ሳያስተካክል ማለፍ የለበትም” ብለዋል በርኔት። “በመጨረሻም ጊዜው በፌዴራል መንግስት ተሳትፎ ሲፈጸሙ የነበሩ መጠነ ሰፊ ወንጀሎች የሚቆሙበት እና ተጠያቂነት የሚጀምርበት ጊዜ መሆን አለበት” ብለዋል።

Your tax deductible gift can help stop human rights violations and save lives around the world.

Region / Country