የኦጋዴን ዕስር ቤት ሳተላይት ካርታ፣h ግንቦት 2016 ኢትዮጵያ

“ልክ እንደ ሞቱት ነን”

ሰቆቃ እና ሌሎች ግፎች በኢትዮጵያ ሶማሌ ክልል ኦጋዴን እስር ቤት ዉስጥ

የኦጋዴን ዕስር ቤት ሳተላይት ካርታ፣h ግንቦት 2016 ኢትዮጵያ © CNES 2018 - Airbus DS 2018; Source Google Earth

 

ማጠቃለያ

የኦጋዴን እስር ቤት ከምታስበው በላይ ነው። እጅህ ተይዞ ከታሰርክበት እለት አንስቶ እስከምትፈታበት ቀን ድረስ በህይወት መኖር አለመኖርህን እርግጠኛ መሆን አትችልም። ቀን እና ሌሊት ትደበደባለህ፣ ትዋረዳለህ፣ በረሃብ ትሰቃያለህ። ከእስር ቤቱ መጨናነቅ የተነሳ መተኛት አይቻልም።

መሀመድ የቀድሞ እስረኛ- እድሜ 42፣ ለ ፭ ዓመታት ያለ አንዳች ክስ ታስሮ የቆየ- ነሃሴ 2018

በጅግጅጋ ከተማ እምብርት ከጅግጅጋ ዩንቨርሲቲ በ5 ደቂቃ ርቀት ላይ ከኢትዮጵያ እስር ቤቶች በአሰቃቂነቱ በጣም የታወቀው የጅግጅጋ ማዕከላዊ እስር ቤት ይገኛል፡፡ ይሄ በተለምዶው የኦጋዴን እስር ቤት በማባል የሚታወቀው ቦታ ግፍ እና መከራ የተፈራረቀባቸ እስር ቤት ዉስጥ የተረሱ በሺዎች የሚቆጠሩ እስረኞች መኖሪያ ቦታ ነው።በኦጋዴን እስር ቤት የሚገኙት ብዙዎቹ እስረኞች ምንም አይነት ክስ አልተመሰረተባቸዉም፣ ፍርድ ቤትም ቀርበው አያውቁም።

የቀድሞ እስረኞች በእስር ቤቱ ዉስጥ ያልተቋረጠ ግፍ፣ሰቆቃ፣ ድብደባ፣ ማዋረድ እንደተፈጸመባቸው ምስክርነት ሰጥተዋል። በቂ ያልሆነ የህክምና አገልግሎት፣ በቂ ያልሆነ የቤተሰብ እና የጠበቃ ጉብኝት ይባስ ብሎ አንዳንዴም በቂ ምግብ ያለማግኘትም ዋና ዋና የእስረኞቹ ችግሮች ናቸው፡፡ የመንግስት ባለስልጣናት እስረኞችን በሌሎች እስረኞች ፊትለፊት ልብሳቸዉን አስወልቀው ራቁታቸዉን ይደበድቧቸዋል፣ ይህንንም የሚያደርጉት ለማዋረድ እና ሌሎች እስረኞች እንዲፈሩ እና እንዲሸማቀቁ ለማድረግ ነው። በእስረኞች በተጨናነቀው እስር ቤት ዉስጥ ካፖ የሚባሉ የየክፍሉ አለቆች እስረኞችን ሌሊት ሌሊት እየደበደቡ መረጃ ተቀብለው ለማረሚያ ቤቱ ሀላፊዎች ያስተላልፋሉ። በዚያ መረጃ ላይ በመመስረትም ሀላፊዎቹ ለበለጠ ቅጣት እስረኞችን ይመለምላሉ። የዚህ ሁሉ ማሰቃየት እና ግፍ አላማ እስረኞቹ በህግ የታገደው የኦጋዴን ነጻ አዉጪ ግንባር (ኦብነግ) አባል መሆናቸዉን እንዲያምኑ ለማስገደድ ነው።

ይህ ሶማሌ ክልል በሚገኘው የኦጋዴን እስር ቤት ዉስጥ ከ2011 (እኤአ) እስከ 2018 (እኤአ) የተከናወኑ የማሰቃየት፣ የመደብደብ፣ በዘፈቀደ የማሰር እና የመደፈር የመብት ጥሰቶችን የሰነደው ሪፖርት የተዘጋጀው ከ70 በላይ የቀድሞ የኦጋዴን እስር ቤት እስረኞችን ጨምሮ 100 ቃለ-መጠይቆች መሰረት በማድረግ ነው፡፡በቃለ-መጠይቁ ዉስጥ የመንግስት ባለስልጣናት እና የሶማሌ ልዩ ፖሊስ አባላትም ተሳትፈዋል።

በእስር ቤቱ ዉስጥ የመንግስት ባለስልጣናት በሚያደርሱባቸው ግፍ እና ማሰቃየት የተነሳ እስረኞች መሞታቸዉን በዐይናቸው እንዳዩ ብዙ የቀድሞ እስረኞች ተናግረዋል። የቀድሞ ሴት እስረኞች ደግሞ በእስር ቤቱ ዉስጥ አስገድዶ መደፈር እንደ ደረሰባቸው ምስክርነታቸውን ሰጥተዋል። የማረሚያ ቤቱ የጥበቃ ሰራተኞች እና በጭካኔያቸው የታወቁ የልዩ ፖሊስ አባላት ከክልሉ ከፍተኛ ሀላፊዎች ትዕዛዝ እየተቀበሉ እስረኞቹን አሰቃይተዋል። የጥናቱ ውጤት የሚያሳየው ማረሚያ ቤቱ ምንም አይነት ተጠያቂነት እና ሀላፊነት ያልሰፈነበት ተቋም መሆኑን ነው።

በኦጋዴን እስር ቤት ዉስጥ የሚፈጸመው የማሰቃየት፣ የማሸማቀቅ፣ የእስረኞች መጨናነቅ፣ በቂ የሆነ የእንቅልፍ፣ የምግብ እና የጤና አገልግሎት መከልከል የኦብነግ ደጋፊ ናቸው ተብለው የሚታሰቡ ሰዎችን በጅምላ የመቅጣት አዙሪት አካል ነው። ሂዩማን ራይትስ ዎች በ2007/2008 (እኤአ) የኢትዮጵያ ሰራዊት ኦብነግ ላይ እርምጃ ለመውሰድ በተንቀሳቀሰበት ወቅት በዘፈቀደ መግደል፣ ማሰቃየት እና መድፈርን ጨምሮ ብዙ የሰው ልጅ ላይ የሰራዊቱ አባላት የፈጸሙትን የጦር ወንጀሎች ከዚህ በፊት መዘገቡ ይታወሳል። ይሁን እንጂ መንግስት በዚያ ግዜ የተፈጸሙትን ግፎች ከመመርመር ይልቅ የኢትዮጵያ መንግስት የሶማሌ ልዩ ፖሊስን በ2008 (እኤአ) አቋቋመ። ይሄ ልዩ ፖሊስም ከ2008 (እኤአ) ጀምሮ በሶማሌ ክልል ዉስጥ ዘግናኝ ግፎችን ደጋግሞ የሚፈጽም አደረጃጀት ነው። የልዩ ፖሊስ ተጠሪነት ለክልሉ ፕሬዘዳንት ለአብዲ ሞሃመድ ኦመር በተለምዶ  አብዲ ኢለይ ነው።

በተጨማሪ በኦጋዴን እስር ቤት ዉስጥ በሽታ በብዛት ይከሰታል። እስር ቤቱ ዉስጥ በተከሰተው ወረርሺኝ ሳቢያ እስረኞች መሞታቸው እየተነገረም ቢሆን የመሰረታዊ ዉሃ እና የንጽህና አገልግሎት ጥያቄዎች በዘዴ ችላ ተብለዋል። አንዳንዴ የሞቱት እስረኞች ሬሳ እንኳን ሳይነሳ ብዙ ቀን በእስረኞች ክፍል ዉስጥ እንደሚቆይ የቀድሞ እስረኞች ለህዩማን ራይትስ ዎች ተናግረዋል።

የሴት እስረኞች ያለምንም የጤና እርዳታ በጣም በቆሸሸ ክፍል ዉስጥ እንዲወልዱ ተደርገዋል። እናቶቻቸው በእስር ቤቱ ጥበቃ ሰራተኞች ከተደፈሩ በኃላ ተረግዘው የተወለዱ ህጻናትን ሰቆቃ መስማት እጅግ በጣም ሰቅጣጭ ነው። ጡት የሚያጠቡ እናቶች ምንም አይነት ተጨማሪ ምግብ እንደማያገኙ እና ልጆቻቸዉም የትምህርት ዕድል እንዳላገኙ የቀድሞ እስረኞች ምስክርነታቸው ላይ ተናግረዋል። ከ2013 (እኤአ) ጀምሮ እስረኞች በጠያቂዎች መጎብኘት፣ ከቤተሰብም ምግብ እና ሌሎች ቁሳቁሶችን ማግኘት እንደተከለከሉ ተናግረዋል። የእስረኞች መለቀቅ በዘፈቀደ ከመሆኑም በተጨማሪ ፍርድ ቅጣት ያገኙ እስረኞችም ቢሆኑ የተፈረደባቸው ቅጣትና የሚፈቱበት ቀን ምንም ግንኙነት የለውም፡፡  

አንዳንድ የቀድሞ እስረኞች እንደተናገሩት የሶማሌ ክልል ፕሬዝዳንት አብዲ ኢለይ እና የክልሉ የጸጥታ ሀላፊ እና የልዩ ፖሊስ ሀላፊ አብድርሀማን ለባጎሌን ጨምሮ የክልሉ ከፍተኛ አመራሮች በተደጋጋሚ እስር ቤት ድረስ በመሄድ እስረኞችን ያነጋግራሉ። እነኝህ ባለስልጣናት በእስር ቤቱ የሚገኙት ፣እስረኞች ላይ የሚፈጸመዉን ማሰቃየት ለማዘዝ ብቻ ሳይሆን አንዳንዴ ሴት እስረኞችን ለመድፈር እና እራሳቸው በቀጥታ ለማሰቃያት ተግባር ላይ ለመሳተፍም ጭምር ነው፡፡ የመብት ጥሰቱን እና ግፉን በዋናነት የሚፈጽሙት ደግሞ የኦጋዴን እስር ቤት ሀላፊዎች ናቸው።

በ2011 (እ.ኤ.አ) የሶማሌ ክልል ባለስልጣናት እና የእስር ቤት ጠባቂዎች ለ11 ቀናት የቆየ ግምገማ አድርገው ነበር። በዚህ ግምገማ ላይ የቀድሞ እስረኞች ለሂውማን ራይትስ ዎች የተናገሩትን በሚያረጋግጥ መልኩ የጥበቃ ሰራተኞቹ እራሳቸው የመብት ጥሰቶቹ እንደሚፈጽሙ ደግመው መስክረዋል። ግምገማው እንዲቀረጽ የታዘዘው በክልሉ ፕሬዘዳንት አብዲ ኢለይ ሲሆን ከአመታት በኃላ የአብዲ ኢለይ አማካሪ የነበረው ግለሰብ ከአገር ሲኮበልል ቪድዮዉን ይዞት በመውጣቱ ሂዩማን ራይትስ ዎች ፊልሙን ማግኘት ችሏል፡፡ በፊልሙ ላይ የጥበቃ ሰራተኞቹ እስረኞችን እንዴት ሲያሰቃዩ እንደነበረ፣ እንዴት ሲደፍሩ እንደነበረ፣ ከእስረኞች ገንዘብ እንዴት እንደወሰዱ እና የኦጋዴን እስር ቤት ሀላፊዎች እስረኞች እንዲደፈሩ እና እንዲሰቃዩ ትዕዛዝ ሲያስተላልፉ እንደ ነበር  በዝርዝር ይታያል።

ከ2011 (እኤአ) ጀምሮ የፌዴራል መንግስት አካል የሆነው እና የሰብአዊ መብቶች ጥሰት አቤቱታዎችን እንዲመረምር ኃላፊነት የተሰጠው የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን መርማሪዎች የኦጋዴን እስር ቤትን ብዙ ጊዜ ጎብኝተዋል። ነገር ግን የምርመራ እና የጉብኝት ውጤቱን በተመለከተ ለህዝብ የተገለጸ አንዳችም ሪፖርት የለም። በእስር ቤቱ ዉስጥ የተፈጸሙትን ግፍ እና ማሰቃየቶች ለመቅረፍ እንዲሁም ጥፋተኞችን ለፍትህ ለማቅረብ የተወሰደ የእርምት እርምጃ ስለመኖሩም የታወቀ ነገር የለም። እስረኞች ኮሚሽኑ ወደ እስር ቤቱ በሚመጣበት ወቅት ምን ማለት እንዳለባቸው እና ምን ማለት እንደሌለባቸው አስቀድመው እንደሚነገራቸው የቀድሞ እስረኞች ገልጸዋል። በተጨማሪም መቁሰላቸው በግልጽ የሚታይባቸው እስረኞች፣ እርጉዝ ሴቶች፣ እና ህጻናት ከኮሚሽኑ ጉብኝት አስቀድመው ወደ ሌላ ድብቅ እስር ቤት ወይም ከእስር ቤቱ ዉጪ ተጓጉዘው ይደበቁ እንደነበር የቀድሞ እስረኞች ይናገራሉ። በእስር ቤቱ ዉስጥ ስለሚፈጸሙ ድርጊቶች ለኮሚሽኑ በግልጽነት የተናገሩ እስረኞች ኮሚሽኑ ጉብኝቱን ጨርሶ ከሄደ በኃላ ከባድ ድብደባ ይፈጸምባቸዋል፣ አንዳንዴ ድብደባው እስሞትም ያደርሳል፡፡ሂውማን ራይትስ ዎች በኦጋዴን እስር ቤት ተፈጸሙ የተባሉ ግፎች ለማረም የወሰደ እርምጃ መኖሩን ከኮሚሽኑ ለማጣራት ያደረገው ሙከራ ኮሚሽኑ ምላሽ ባለመስጠቱ ምክንያት አልተሳካም፡፡  

የኢትዮጵያ የፌዴራል አወቃቀር ሶማሌ ክልልን ጨምሮ ብዙ የአስተዳደር ስራዎችን መስራት እንዲችሉ ከፍተኛ ሉአላዊ ስልጣንን ለክልሎች ይሰጣል። የፌደራል መንግስቱ የሶማሌ ክልል እስር ቤቶችን ለመከታተል አቅም የለውም፣ ፍላጎትም አላሳየም። 

ቃለ-መጠይቅ ካደረግንላቸው የቀድሞ እስረኞች መካከል ለፍርድ ቤት ቀርበው የሚያዉቁት ወይንም ክስ የተመሰረተባቸው እጅግ በጣም ጥቂቶቹ ናቸው። ብዙዎቹ ለፍርድ ቤት ሲቀርቡም ምንም አይነት የጠበቃ ድጋፍ አያገኙም። በቂ የመከላከያ ምስክርንም ማቅረብ አይችሉም። በመንግስት የሚፈጽመዉን በደል ለመመርመር እና ለመጠየቅ ፍላጎት በሌላቸው ነጻ ያልሆኑ ፍርድ ቤቶች ብቻቸውን ይቀርባሉ ይህም እነዚህ እስረኞች ከተከሰሱበት ክስ በምንም አይነት ሁኔታ ነጻ እንዳይሆኑ ያግዳቸዋል።

ማሰቃየት እና ለማሰቃየት ወንጀል ተጠያቂነት አለመኖር ኢትዮጵያ ዉስጥ በጣም የተንሰራፋ ችግር ነው። ኢትዮጵያ ዉስጥ በጉልበት መረጃ መሰብሰብ በቋሚነት እንደሚፈጸም ለሂውማን ራይትስ ዎች የሚደርሱት ሪፖርቶች ያሳያሉ። ከባድ ድብደባ፣ ዉሃ ዉስጥ የመዝፈቅ እና ብልትን ማኮላሸት ከምርመራ ዘዴዎቹ ዉስጥ ይገኛበታል። የኦጋዴን እስር ቤት የቀድሞ እስረኞችም የዚህ አይነት ተመሳሳይ ምርመራ እንደተፈጸመባቸው ገልጸዉልናል። ሂውማን ራይትስ ዎች ባሰባሰበው መረጃ መሰረት የኢትዮጵያ መንግስት እስረኞቹ ተፈጽሞብናል ያሉትን የማሰቃየት ተግባር መርምሮ አንድም ሰቆቃ ፈጻሚን ለፍርድ አላቀረበም።

የኢትዮጵያ መንግስት ተፈጸሙ የተባሉት ግፎች እና ሰቆቃዎች እንዲመረመሩ በሚጠየቅበት ወቅት የሚጠው ምላሽ የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን ይሄን ምርመራ የማድረግ ሃላፊነት ይወጣል የሚል ነው፡፡ በተግባር ግን የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን ሪፖርቶች መሰረታዊ የገለልተኛነት እሳቤን እንኳን አያሟሉም። ተቋሙም እስካሁን በስራዎቹ የሚያሳየው ግልጽነትን በጣም የተገደበ ነው ። የኢትዮጵያ መንግስት ተፈጸሙ የተባሉትን ሰቆቃዎች እና የሰብአዊ መብት ጥሰቶችን በተመለከተ ገለልተኛ አለማቀፋዊ አካል እንዲመረምር የተደረገለትን ጥሪ በተደጋጋሚ ሳይቀበለው ቀርቷል፡፡ በተባበሩት መንግስታት ድርጅት የማሰቃያት እና ኢሰብአዊ አያያዝ ልዩ ራፖርተር እና ሌሎች የተለያዩ ስምንት ራፓርተሮች  አገር ውስጥ ገብተው ማጣራት ለማድረግ በተደጋጋሚ ጠይቀውም ተቀባይነት አጥተዋል፡፡

አዲሱ የኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶ/ር አብይ አህመድ ወደ መሪነት የመጡት ሚያዝያ 2018 ነው። ስልጣን ከያዙበት ቀን ጀምሮ በርካታ ተራማጅ መሻሻያዎችን ለመተግባር ቃል ገብተዋል። መንግስታቻው በአዲስ አበባ የሚገኘዉን የብዙ እስረኞች ማሳቃያ የነበረውን ማዕከላዊ እስር ቤትን ዘግቷል። በተጨማሪም በሰኔ ወር 2018 ፓርላማ ዉስጥ የኢትዮጵያ መሪዎች አምነው ይቀበሉታል ተብሎ በማይታሰብ መልኩ ኢትዮጵያ ዉስጥ ማሰቃየት እንደሚፈጸም አምነው ተናገረዋል፡፡

ነገር ግን ጠቅላይ ሚንስትሩ እስከ አሁን ግን በሀገሪቱ የተንሰራፋዉን ማሰቃየት እና የተጠያቂነት መጥፋት መንግስታቸው በምን መልኩ ለመቅረፍ እንደ ተዘጋጀ ያሉት ነገር የለም። የኦጋዴን እስር ቤት ቢዘጋ የቀድሞ እስረኞችን ማስደሰት ቢችልም፣ እንደዚህ አይነት እርምጃዎች የክልሉ የጸጥታ ሀይሎችን ግፈኝነት እና ለፈጸሙት ወንጀል ያለመጠየቅን እንዲሁም በሶማሌ ክልል የሰፈነዉን ደካማ የሕግ የበላይነትን ችግር ልቀርፍ አይችልም።

ኢትዮጵያ በራሷ ሕገመንግስት ዉስጥ የደነገገቻቸውን መብቶች ማክበር እና በአለማቀፉ የሰብአዊ መብቶች ድንጋጌ ዉስጥ የፈረመቻቸውን ግዴታዎች መወጣት አለባት። በተለይ ማሰቃየትን፣ ኢሰብአዊ እና አዋራጅ አያያዝን ፈጽሞ በመከልከል በስፋት የተዘገበዉን ሰቆቃ እና ህገ-ወጥ እስራትን ማስቀረበት ወሳኝ ነው። አዲሱ የኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚንስትር፣ ከፍተኛ የመንግስት ባለስልጣናት፣ የፌዴራል ፖሊስ እና መከላከያው በአስቸኳይ እና በግልጽ በኦጋዴን እስር ቤት እና በሁሉም የኢትዮጵያ እስር ቤቶች ዉስጥ የሚፈጸመዉን ሰቆቃ በማውገዝ ተገቢ ያልሆነ የእስረኞች አያያዝ መታገስ እንደሌለባት ጠንከር ያለ መልእክት ማስተላለፍ አለባቸው። አክለውም ሰቆቃ ፈጸሚዎቹን ባለስልጣናት ህግ ፊት በማቅረብ የመግለጫዉን ተግባራዊነት ሊያረጋግጡ ይገባል።

ዘግናኝ ሁኔታዎች በሚሰሙበት በዚህ ወቅት ዶ/ር አብይ አህመድ እና የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በሶማሌ ክልል የተደረጉ የመብት ጥሰቶችን የሚያጣራ የፌዴራል መንግስት አጣሪ ኮሚሽንን ማቋቋም አስፈላጊ ነው። ይሄው ኮሚሽን በኦጋዴን እስር ቤት ተፈጽመዋል የተባሉትን የመብት ጥሰቶችን በመመርመር በሁሉም የስልጣን እርከን ላይ ያሉት የመንግስት ሀላፊዎች በእስረኞች ላይ ግፍ የፈጸሙት ተለይተው በወንጀል እንዲጠየቁ ማድረግ ይኖርበታል፡፡ ይሄ ምርመራ የሶማሌ ክልል ፕሬዝዳንት አብዲ ኢለይን እና የሶማሌ ልዩ ፖሊስ ሀላፊ አብድርሃማን ለባጎሌን የመሳሰሉ ከፍተኛ ባለስልጣናትንም ማካተት አለበት።

ከላይ የተጠቀሱት እንዳሉ ሆነው የኦጋዴን እስር ቤት ለገለልተኛ ኢትዮጵያዊ እና ለአለማቀፋዊ ተቋማት፣ ለሰብአዊ መብት ተቋማት፣ ለሰብአዊ እርዳታ ለጋሾች፣ ለአፍሪካ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን፣ ለተባበሩት መንግስታት ልዩ የሰቆቃ እና ሌሎች ኢሰብአዊ አያያዝ ራፖርተር፣ እንዲሁም ለህገ-ወጥ እስራት ተከታታይ የስራ ቡድን እና ለዲፕሎማቲክ ኮምዮኒቲ በሩን ክፍት በማድረግ እንዲጎበኝ ሊፈቀድ ይገባል፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ የሶማሌ ክልል ልዩ ፖሊስን በፍጥነት ማደስና የልዩ ፖሊስ እና የሶማሌ ክልል ከፍተኛ አመራሮችን የኦጋዴን እስር ቤት ዉስጥ ለተፈጸሙት ማሰቃየትን እና ሌሎች የሰብአዊ መብቶች ጥሰት ተጠያቂ ሊያደርጓቸው ይገባል።

ምክረ-ሀሳብ

በዚህ ጥናት ግኝቶች ላይ መሰረት አድርጎ ሂውማን ራይትስ ወች የሚከተሉትን ምክረ ሃሳቦች ለሚመለከታቸው አካላት ያቀርባል፡፡

ለኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚንስትር

 • በኢትዮጵያ ዉስጥ የሚፈጸሙትን ማሰቃየት እና ሌሎች አዋራጅ እና ኢሰብአዊ አያያዞችን በማያሻማ መልኩ በግልጽ እንዲያወግዙ እንዲሁም በምንም አይነት መልኩ የማሰቃየት ተግባር መፈጸም ተቀባይነት እንደሌለው በማያሻማ መልኩ መልእክታቸውን እንዲያስተላልፉ
 • በኦጋዴን እስር ቤት ዉስጥ የተፈጸሙትን ግፎች የሚያጠና የፈዴራል ባለሙያዎች ኮሚሽን እንዲቋቋም ድጋፍ እንዲያደርጉ፤  ኮሚሽኑ የሚከተሉትን ስራዎችን መስራት እንዲችል እገዛ እንዲያደርጉ
  • በኦጋዴን እስር ቤት ዉስጥ የሚገኙ እስረኞችን ጉዳይ መገምገም እና የሚከተሉትን እርምጃዎች ቢወስዱ፥
   • የእስር ግዜያቸውን የጨረሱት እንዲፈቱ
   • እስካሁን ክስ ያልተመሰረተባቸው እስረኞች በተጨባጭ ማስረጃ የተደገፈ ክስ በፍጥነት እንዲመሰረትባቸው ወይንም በቶሎ እንዲለቀቁ
   • የተከሰሱት እስረኞችም እራሳቸዉን ራሳቸዉን መከላከል እንዲችሉ የጠበቃ እገዛ አና ነጻ ፍርድ ቤት እንዲያገኙ።
 • እስረኞቹ ጉዳያቸው በሚታይበት ወቅት የሚያቀርቡትን የመሰቃየት አቤቱታ መመርመር እና፤
 • በየትኛዉም የመንግስት እርከን ላይ የሚገኙ እስረኞችን ያሰቃዩ ሃላፊዎች በወንጀል እንዲጠየቁ ቢደረግ፣  ምርመራውና በወንጀል መጠየቁ የመብት ጥሰቱን በቀጥታ ያዘዙና፣ የፈጸሙትን ጨምሮ የእስር ቤቱ ሀላፊዎችን ማካተት አለበት።
 • የፌዴራል ኮሚሽን ማቋቋም ባልተቻለበት ሁኔታ ጠቅላይ ሚንስትሩ ተፈጸሙ የተባሉትን ኢሰብአዊ አያያዝ እና ማሰቃየት እንዲጣራ በፍጥነት ግልጽ እና ገለልተኛ ምርመራ በማዘዝ ይሄን ሰቆቃ የፈጸሙት ሁሉም የመንግስት ባለስልጣናት ለፍርድ እንዲቀርቡ እና እንዲቀጡ እንዲያደርጉ   
 • የምርመራ ሂደቱን እና ግፍ ፈጻሚዎቹ ላይ ስለ ተወሰደው እርምጃ መደበኛ ሪፖርት ለህዝብ ይፋ ቢደረግ
 • በሌሎች የኢትዮጵያ ክፍሎች ያሉ የልዩ ፖሊሶችን ስልጣን እና ሀላፊነትን የግልጽ የሚስቀምጥና የሚገድብ ህግ ከፓርላማው ጋር በመስራት ተረቅቆ እንዲጸድቅ መደረጉን እንዲያረጋግጡ
 • የሶማሌያ ክልል ልዩ ፖሊስን በሰፊው ማደስ እና የአመራሩን እና አዛዦቹን ሀላፊነት በግልጽ መወሰን እንዲሁም በሰፊ መብት ጥሰት የተሳተፉትን የልዩ ፖሊስ ቡድኖች እንዲበተኑ እንዲያደርጉ
 • አሰራሮችን በማሻሻል እና የበጀት ምደባን በማስተካከል የኢትዮጵያ ማረሚያ ቤቶች መሰረታዊ የተባበሩት መንግስታት የእስረኞች አያያዝ መመዘኛ እንዲያሟሉ ጥረት እንዲያደርጉ
 • የኦጋዴን እስር ቤት እና ሌሎች እስር ቤቶች በገለልተኛ የሰብአዊ መብቶች ቡድን ክትትል እንዲደረግባቸው መፍቀድ ፣ ይሄ ፍቃድ እስረኞችን በሚስጥር እና ሶስተኛ አካል በሌለበት ምስክሮችን ያካተተ መሆኑን በተረጋገጠ መልኩ መካሄዱን እንዲያረጋግጡ   
 • የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የማሰቃየት፣ አሸማቃቂ እና የኢሰብአዊ አያያዝ ልዩ ራፖርተርን እና የህገ ወጥ እስራት ተከታተይ የስራ ቡድንን ጨምሮ ጉዳዩ የሚመለከታቸዉን የተባበሩት መንግስታት ድርጅቶች እና የአፍሪካ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን የስራ ቡድኖች የጉብኝት ፈቃድ እንዲሰጣቸው ቢደረግ    

ለኢትዮጵያ ፓርላማ

 • ከጠቅላይ ሚኒስትሩ ጋር በመሆን ከላይ የተጠቀሰዉን የፌዴራል የባለሞያዎች ቡድን ቢያቋቁም
 • እስረኞች መደበኛ የጠበቃ ድጋፍ እንዲያገኙ እና ፍርድ ቤት ሳይቀርቡ ረዥም ግዜን በእስር እንዳያሳልፉ እና በድብደባ እና ማሰቃየት የተገኘው የትኛዉም ማስረጃ ህግ ፊት ተቀባይነት እንዳይኖረው የመረጃ አሰባሰብ ደንብን በግልጽ ቢያስቀምጥ፣  ሀገሪቱ የፈረመቻቸዉን አለማቀፍ ድንጋጌዎች ጋር የሚጋጭን የኢትዮጵያ የወንጀለኛ መቅጫ ህግ ይዘቶችን እንዲሻሻሉ ቢያደርግ
 • በሶማሌ ክልል በሚገኙ ሁሉም እስር ቤቶች ዉስጥ የፌዴራል መንግስት ክትትል እንዲኖር ቢያደርግ
 • የፌዴራል ፖሊስ፣ መከላከያ፣ የክልል ፖሊሶች፣ ልዩ ፖሊሶች፣ የማረሚያ ቤት የጥበቃ ሰራተኞች እና ሌሎች የህግ አስፈጻሚ አካላት አለማቀፍ የሰብአዊ መብቶች መመዘኛ የማይጥስ የምርመራ አሰራሮችን እንዲከተሉ በቂ ስልጠና መሰጠቱን እንዲያረጋግጥ
 • አለማቀፍ ድንጋጌዎች የጸረ ሰቆቃ የሰብዐዊ ክብር ማዋረድን፣ ኢሰብአዊ አያያዝ እና ቅጣት እንዲሁም የፖለቲካ እና የሲቪል ቃል ኪዳን አማራጭ በመፈረም የአገሪቱ ህግ ውስጥ መካተቱን እንዲያረጋግጥ  

ለኢትዮጵያ ሰብአዊ መብት ኮሚሽን

 • የኦጋዴን እስር ቤትን እና ሌሎች ማቆያ ቤቶችን በተደጋጋሚ እና በሚስጥር በመጎብኘት ሶስተኛ ሰው በሌለበት ምስክሮችን እንዲያነጋግር
 •  ለቃለምልልስ ለመስጠት አነስተኛ ስጋት ያለባቸውን የኦጋዴን እስር ቤት የቀድሞ እስረኞች በመጠየቅ የተፈጸሙባቸውን ግፍ እንዲያጣራ እና ክትትል እንዲያደርግ
 • እስረኞች ከኮሚሽኑ ጉብኝት በኃላ የበቀል እርምጃ እንዳይወሰድባቸው ከኮሚሽኑ ጋራ የተነጋገሩ እስረኞች ደህንነት ላይ ከፍተኛ ጥንቃቄ ማድረግ ፣ የሚያነጋግራቸዉን እስረኞች የሚመርጠው እራሱ ኮሚሽኑ ብቻ መሆኑን ማረጋገጥ
 • የእስረኞች አያያዝን እና የእስር ቤቶችን ሁኔታ በተመለከተ ሪፓርቶች ይፋ እንዲያደርግ
 • የኦጋዴን እስር ቤት ጉብኝት ሪፖርቶች በእስር ቤቱ አያያዝን ለማሻሻል የተወሰደ እርምጃ ካለ እና ግፍ ፈጻሚዎችን ተጠያቂ የማድረግ ስራ ከተሰራ ይፋ እንዲያደርግ

ለተባበሩት መንግስታት የሰብአዊ መብቶች ካዎንስል

 • በሶማሌ ክልል እና በመላው ኢትዮጵያ ከህግ ዉጪ ታስረው የሚገኙ እስረኞች እንዲለቀቁ ግፊት ማድረግ
 • ኢትዮጵያ የተባበሩት መንግስታት ልዩ የሰቆቃ እና ሌሎች ኢሰብአዊ ኣያያዝ ራፖርተር፣ እንዲሁም ለህገወጥ አስራት ተከታታይ የስራ ቡድን ወደ ሀገሪቱ ገብቶ ጉብኝት እንዲያደርጉ መወትወት።
 • በኢትዮጵያ መቆያ ቤቶች ዉስጥ እየተፈጸሙ ያሉ ማሰቀያት ላይ ተዐማኒ፣ ገለልተኛ እና ግልጽ ምርመራ ማድረግ  

ለአለማቀፍ የኢትዮጵያ አጋሮች

 • በኦጋዴን እስር ቤት ዉስጥ እና በመላው ሀገሪቱ ማቆያ ቤቶች ስለሚፈጸመው ማሰቃየት፣ ክፉ አያያዝ እና ሌሎች የሰብአዊ መብቶች ጥሰትን በግልም በይፋም ለኢትዮጵያ መንግስት ማንሳት  
 • የጸጥታ ሀይሎችን በገንዘብና የሚያግዙ ለጋሾች ጸጥታ ሀይሎቹ ይፈጽማሉ የተባሉትን አቤቱታዎች በመመርመር በጀታቻው ለመብት ጥሰት እንደማይውል ማረጋገጥ
 • የአለማቀፍ የሰብአዊ እርዳታ ድርጅቶች እና የሰብአዊ መብት ተሟጋች ድርጅቶች የእስረኞችን አያያዝ እንዲገመግሙ እና ህገወጥ እስራትን መከታተል ይችሉ ዘንድ ያለምንም ክልከላ እስር ቤቶችን እንድጎበኙ መጠየቅ
 • ኢትዮጵያ መንግስት የተባበሩት መንግስታት ልዩ የሰቆቃ እና ሌሎች ኢሰብአዊ ኣያያዝ ራፖርተር፣ እንዲሁም ለህገወጥ አስራት ተከታታይ የስራ ቡድን ወደ ሀገሪቱ ገብቶ ጉብኝት እንድያደርጉ እንዲፈቅድ መጠየቅ
 • ተፈጸሙ የተባሉት ኢሰብአዊ አያያዝ እና ማሰቃየት እንዲጣሩ እና ፈጣን ግልጽ እና ገለልተኛ ምርመራ እንዲደረግ መጠየቅ
 • ለሶማሌ ክልል ከተመደበው በጀት ምን ያህሉ የሰብአዊ መብት ጥሰት እያደረሱ ለሚገኙት ልዩ ፖሊስ ሃይል አባላት እንደሚደርስ ምርመራ ማካሄድ
 • የኢትዮጵያ መንግስት ግፈኛዉን የሶማሌ ልዩ ፖሊስ ተቋም እንዲያድስ ግፊት ማድረግ

ለተባበሩት መንግስታት ድርጅት የሰቆቃ እና ሌሎች ኢሰብአዊ እና አዋራጅ ኣያያዝ ወይም ቅጣት ልዩ ራፖርተር፣ እና ለህገ-ወጥ እስራት ተከታታይ የስራ ቡድን

 • የኢትዮጵያ መንግስት ጥሪ እንዲያደርግ መወትወት፣ መንግስት ጥሪ ማድረጉ ካልተሳካም አማራጭ የመረጃ ምንጭ በመጠቀም ሪፖርት ማድረግ

ለተበባሩት መንግስታት ድርጅት የዳኞች እና ጠበቆች ነጻነት ልዩ ራፖርተር

 • በተለይ የሶማሌ ክልል ላይ ትኩረት በማድረግ ኢትዮጵያ ዉስጥ ያለዉን የፍርድ ቤቶች ነጻነት ለመመርመር ከኢትዮጵያ መንግስት የጉብኝት ግብዣ መጠየቅ፣ ይህ ባልተሳካበት ሁኔታ አማራጭ የመረጃ ምንጭ በመጠቀም ሪፖርት ማድረግ

ለአፍሪካ የሰብአዊ እና የህዝብ መብቶች ኮሚሽን የእስር ቤት ሁኔታዎች እና ማቆያ ማዕከላት እና የፖሊስ ልዩ ራፖርተር

 • በሶማሌ ክልል የኦጋዴን እስር ቤትን ጨምሮ ኢትዮጵያ ዉስጥ የሚገኙ እስር ቤቶችን እና ማቆያ ማዕከላት ዉስጥ የሚፈጸመውን የማሰቃያት እና ሌሎች ኢሰብአዊ የእስረኞች አያያዝ ለመመርመር ከኢትዮጵያ መንግስት የጉብኝት ግብዣ መጠየቅ።