(ናይሮቢ፤ ሰኔ 9 ቀን 2008 ዓ.ም) – ከህዳር ወር 2008 ዓ.ም. ጀምሮ በኦሮሚያ ክልል በተካሄዱ የተቃውሞ ሰልፎች የኢትዮጵያ መንግስት የጸጥታ ሀይሎች ከ400 በላይ የሚሆኑ ሰልፈኞችን የገደሉ ሲሆን ከአስር ሺህ በላይ የሚቆጠሩትን ደግሞ ማሰራቸውን ሂዩማን ራይት ወች ዛሬ ይፋ ባደረገው ሪፖርት ገለጸ፡፡ የኢትዮጵያ መንግስት የተፈጸሙ ግድያዎችን፣ እስራቶችንና ሌሎች የመብት ጥሰቶች በአስቸኳይ ተአማኒነት ያለውና ገለልተኛ የሆነ ማጣሪያ እንዲካሄድ ድጋፍ ማድረግ አለበት።
ይህ ባለ 61 ገጽ ሪፖርት "'ጭካኔ የተሞላበት አፈና' – የግድያ እና የእስራት ምላሽ፤ ለኢትዮጵያ የኦሮሞ ተቃውሞ" የተሰኘው ሪፖርት የኢትዮጵያ መንግስት ተቃውሞሙን ለመቆጣጠር የተጠቀመውን ከመጠን ያለፈ ሀይል እርምጃና እስከ መግደል የሚያደርስ ሃይል፣ የጅምላ እስር፣ ጭካኔ የተሞላበት የእስር ቤት አያያዝ፣ እንዲሁም የተቃውሞ ሂደቶችን በተመለከተ መረጃዎች ለህዝብ እንዳይሰራጩ ማፈንን አጠቃሎ በዝርዝር አቅርቧል፡፡
ይህን ሪፖርት ለማጠናቀር ሂዩማን ራይትስ ዎች እ.ኤ.አ. ከህዳር ወር 2015ዓ.ም. ጀምሮ እስከ ግንቦት 2016 ዓ.ም. ድረስ በሰላማዊ ሰልፈኞች ላይ እንዲሁም ሀሳባቸውን በነጻነት በሚገልጹ ዜጎች ላይ በመንግስት የጸጥታ ሀይሎች የተወሰደውን እርምጃ አስመልክቶ በሀገር ውስጥና ከሀገር ውጪ የሚገኙ ኢትዮጵያውያንን፣ ከ125 በላይ የሚሆኑ የተቃውሞ ሰልፎች ተሳታፊዎችን፣ ጉዳዩን በአንክሮ ሲከታተሉ የቆዩ ግለሰቦችን፣ በተለያዩ ጊዜያት የመብት ጥሰት የተካሄደባቸውና ጉዳት የደረሰባቸውን ግለሰቦች ያካተተ ቃለ መጠይቅ አድርጓል።
"የመንግስት የጸጥታ ሀይሎች ሰብአዊነት በጎደለው ሁኔታ የተቃውሞ ሰልፈኞች ላይ በቀጥታ በመተኮስ በመቶዎች የሚቆጠሩ ተማሪዎችን፣ ገበሬዎችን እና ሌሎች የሰላማዊ ሰልፍ ተሳታፊዎችን ገድለዋል።" በማለት የሂይውማን ራይትስ ወች የአፍሪካ ዳይሬክተር ሌስሊ ሌፍኮው ተናግረዋል። ሌፍኮው አያይዘውም "መንግስት ያለ አግባብ የታሰሩትን በአስቸኳይ መፍታት አለበት፣ ተአማኒነት ያለው እና ገለልተኛ የማጣራት ሂደት እንዲከናወን ድጋፍ ማድረግ አለበት፣ እንዲሁም ይህን ጥቃት የፈጸሙት የጸጥታ ሀይል አባላት ላደረሱት የመብት ጥሰት ተጠያቂ መሆን አለባቸው፡፡"
ሂዩማን ራይትስ ወች የመንግስት የጸጥታ ሀይሎች ለወራት ያህል በኦሮሚያ ክልል የተለያዩ አካባቢዎች በተካሄዱ ተቃውሞዎች ሰልፈኞችን ለመቆጣጠር ቀጥታ መተኮሱን እና በእያንዳንዱ የተቃውሞ ሰልፍ ላይ ቢያንስ ሁለትና ከዚያ በላይ የሆኑ የተቃውሞ ሰልፈኞችን መገደላቸውን አረጋግጧል። ሂዩማን ራይትስ ዎች እና ሌሎች ድርጅቶች ከ300 በላይ የተገደሉ ሰዎችን ማንነት በስም ለይቷል እንዲሁም በተወሰኑት ጉዳይ ላይ በፎቶ ለማረጋገጥ ችሏል።
እ.ኤ.አ. የህዳሩ ተቃውሞ የተቀሰቀሰው መንግስት የዋና ከተማውን የማዘጋጃ ቤት ድንበር በአደሲ አበባ የተቀናጀ ማስተር ፕላን መሰረት ለማስፋፋት ማቀዱን ተከትሎ በተፈጠረ አሳሳቢ ሁኔታ ነው፡፡ ተቃውሞ አድራጊዎቹ ማስተር ፕላኑ የአካባቢውን አርሶ አደሮች ያፈናቅላል እንዲሁም በአካባቢው የእርሻ መሬት ላይ አሉታዊ ተጽዕኖ ያሳድራል፤ የሚጠቅመው ጥቂት የበላዮችን ብቻ ነው የሚል ስጋት ያደረባቸው ሲሆን የማፈናቀል ተግባሩ ባለፈው አስር ዓመት እየጨመረ የመጣ ጉዳይ ነው፡፡
እ.ኤ.አ. በታህሳስ ወር ተቃውሞው ሲስፋፋ መንግስት ተቃውሞውን ለማፈን የጦር ሀይሉን በመላው የኦሮሚያ ክልል ውስጥ አስፍሯል። የጸጥታ ሀይሎች ምንም አይነት ቅድመ ማስጠንቀቅያ ሳይሰጡ ወይም ጉዳት የማያስከትሉ የአድማ መበተኛ መሳሪያ ሳይጠቀሙ ወደ ሰልፈኖች በቀጥታ ተኩሰዋል። በዚህም አይነት ሁኔታ ከተገደሉት ሰልፈኞች መካከል አብዛኞቹ ተማሪዎችና እድሜያቸው ከ18 አመት በታች የሆኑ ታዳጊዎች ናቸው።
የፌደራል ፖሊስ እና የጦር ሰራዊት በጋራ በመሆን በአስር ሺህ የሚቆጠሩ ተማሪዎችን፣ መምህራንን፣ ሙዚቀኞችን፣ የተቃዋሚ አባላትን፣ የጤና ባለሙያዎችን፣ እንዲሁም ለተቃውሞ ሰልፈኞቹ እርዳታ ያደረጉ ወይም በፍርሀት በመሸሽ ላይ ለነበሩ ተማሪዎች መደበቅያ ያዘጋጁ ሰዎችን በሙሉ አስረዋል። በርካታ ታሳሪዎች የተፈቱ ቢሆንም አሁንም ድረስ ቁጥራቸው በውል የማይታወቁ እስረኞች ምንም አይነት ክስ ሳይቀርብባቸው፣ ከህግ አማካሪዎች እና ከቤተሰቦቻቸው ጋር ፈጽሞ መገናኘት እንዳይችሉ ተደርገው ዛሬም ድረስ በተለያዩ እስር ቤቶች ውስጥ ይገኛሉ።
የአይን እማኞች የእስራቱን መጠንና ስፋት 'ከዚህ በፊት ፈጽሞ ታይቶ የማይታወቅ' ሲሉ ገልጸውታል። ነዋሪነቱ በወለጋ ዞን የሆነ ዮሴፍ የተባለ የ52 አመት ሰው "ሙሉ እድሜዬን እዚሁ ነው የኖርኩት። እንዲህ አይነት ጭካኔ የተሞላበት የግፍ ድርጊት በህይወቴ አይቼ አላውቅም፡፡ በየቀኑ እስራት እና ግድያ በህዝባችን ላይ ይፈጸም የነበረ ሲሆን ከእያንዳንዱ ቤተሰብ ውስጥ ቢያንስ አንድ ልጅ ታስሮ ነበር" ብሏል።
ከዚህ ቀደም ታስረው የነበሩ ግለሰቦች በእስር ቤቶች ውስጥ ከፍተኛ ስቃይና የሰባዊ መብት ጥሰቶች እንደተካሄዱባቸው እንዲሁም ሴት ታሳሪዎች አስገድዶ መድፈር እና ጾታዊ ጥቃቶች ይፈጸምባቸው እንደነበር ለሂዩማን ራይት ወች ተናግረዋል። ጥቂቶች እግራቸው የፊጥኝ ታስሮ የቁልቁሊት በመዘቅዘቅ መደብደባቸውን የገለጹ ሲሆን ሌሎች ደግሞ በኤሌክትሪክ እግራቸው ስር መነዘራቸውን ገልጸዋል፤ እንዲሁም በዘር ፍሬያቸው (ብልታቸው) ላይ ክብደት ያለው ነገር ታስሮባቸው እንዲሰቃዩ መደረጋቸውንም ተናግረዋል። በዩኒቨርስቲ ካምፓሶች ውስጥ ታማሪዎች ሲደበደቡ እንደነበር የሚያሳይ ቪዲዮም ታይቷል።
ከጅምላ እስራቱ ባሻገር የመንግስት ባለስልጣናት በጥቂት ግሰቦች ላይ ክስ በመመስረት ፍርድ ቤት አቅርበዋቸዋል። ከፍተኛ ቁጥር ያላቸው የተቃዋሚ ፓርቲ አባላት እና ጋዜጠኞች በአወአዛጋቢው የኢትዮጵያ ጸረ ሽብርተኝነት ህግ የተከሰሱ ሲሆን
አዲስ አበባ በሚገኘው የአሜሪካ ኤምባሲ ፊት ለፊት በመገኘት ሰላማዊ ተቃውሞ ያደረጉ 20 ተማሪዎች በወንጀለኛ መቅጫ ህጉ መሰረት ክስ ተመስርቶባቸዋል።
የመንግስት የጸጥታ ሀይሎች በየትምህርት ቤቱ በመስፈራቸው እንዲሁም በርካታ መምህራንና ተማሪዎች በመታሰራቸውና ቀሪዎቹም ወደ ትምህርት ገበታ ለመመለስ በፍርሀት በመዋጣቸው የተነሳ ተቃውሞው በተካሄደባቸው ብዙ ስፍራዎች ላይ የመማር ማስተማር ሂደቱ ከአንደኛ ደረጃ እስከ ዩኒቨርስቲ ድረስ ሙሉ በሙሉ ተቋርጧል። በአንዳንድ አካባቢዎችም ተቃውሞው እንዳይቀጥል በመስጋት ለስልጣን አካላት ትምህርት ቤቶችን ለሳምንታት ያህል እንዲዘጉ አድርጓል። በርካታ ተማሪዎች ለሂዩማን ራይት ወች እንደተናገሩት ወታደሮች በየትምህርት ቤቱ ቅጥር ጊቢ ውስጥ የሰፈሩ ከመሆኑም ባሻገር የኦሮሞ ብሄር ተወላጆችን ለይተው ከመቆጣጠር አልፈው የመብት ጥሰት ሲያደርጉባቸው ነበር።
አንዳንድ ተአማኒነት ያላቸው ዘገባዎች እንደጠቀሱት በተቃውሞ ሰልፈኞቹም የተካሄዱ የወንጀል ድርጊቶች እንደነበሩ ተስተውሏል፤ ከእነዚህም መካከል የውጭ ሀገር ዜጎች ንበረቶች ወድመዋል፣ የመንግስት ህንጻዎች ተዘርፈዋል፣ እንዲሁም ሌሎች የመንግስት ንብረቶች ወድመዋል። ይሁን እንጂ ሂዩማን ራይት ወች ባደረገው ማጣሪያ እ.ኤ.አ. ከህዳር ወር ጀምሮ በተካሄዱት ከ500 በላይ የተቃውሞ ሰልፎች አብዛኞቹ ፍጹም ሰላማዊ ነበሩ።
የኢትዮጵያ መንግስት በገለልተኛ የሰብአዊ መብት ተሟጋች ተቋማትና በመገናኛ ብዙሀን የጣለው ጽኑ እቀባ ምክኒያትችግሮቹ በሚታዩባቸው ስፍራዎች ላይ ስላለው ሁኔታ የሚወጡት መረጃዎች እጅግ አነስተኛ እንዲሆኑ አድርጓቸዋል። የኢትዮጵያ መንግስት የመገናኛ ብዙሀን ነጻነትን ለማፈን የሚያደርገውን ጥረት ጨምሯል። በዚህም ከመጋቢት ወር አጋማሽ ጀምሮ ፌስ ቡክንና ሌሎች ማህበራዊ ድረ ገጾችን ገድቧል። ከዚህም በተጨማሪ መቀመጫቸውን ከሀገር ውጪ ያደረጉና በሀገር ውስጥ የሚሰራጩ የቴሌቪዥን ጣቢያዎችን አፍኗል።
በጥር ወር ላይ መንግስት የአዲስ አበባን ማስተር ፕላን ሙሉ በሙሉ ማቋረጡን ይፋ አድርጓል። ይሁን እንጂ በወቅቱ መንግስት በወሰደው የሀይልና የግፍ እርምጃዎች ሳቢያ የተቃውሞው አድራጊዎቹ ብሶት ግንፍሎ ወጥቶ ነበር።
እንደ ሂዩማን ራይት ወች ጥናት ከሆነ ከሚያዝያ ወር ጀምሮ በተለያዩ ስፍራዎች ይካሄዱ የነበሩ ተቃውሞዎች እየተቀዛቀዙ የነበረ ቢሆንም የመንግስት የጸጥታ ሀይሎች የሚፈጽሙት አፈና ግን ቀጥሏል። ላለፉት ሰባት ወራት ያህል የታሰሩት በርካቶች አሁንም በእስር ላይ ያሉ ሲሆን ሌሎች በመቶ የሚቆጠሩት ደግሞ የት እንደደረሱ ለማወቅ አልተቻለም፤ ይህም በሀይል እንዲሰወሩ ሳይደረጉ አይቀርም የሚል ስጋት ፈጥሯል። መንግስት ስለቀረበበት በዚህ ሁሉ ውንጀላ ምንም አይነት ተአማኒነት ያለው የማጣራት ስራ አልሰራም። ወታደሮች አሁንም በአንዳንድ ዩኒቨርስቲዎች እንደሰፈሩና በአካባቢውም ከፍተኛ ፍርሀት እንደነገሰ ነው። ተቃውሞ አድራጊዎቹ ምንም እንኳ በመጠኑ አነስተኛ ቢሆንም እ.ኤ.አ. በ2014 ዓ.ም በኦሮሚያ ክልል ተነስቶ የነበረውን የተቃዎሞ ጥያቄ ነው ያስተጋቡት፣ እናም የመንግስት ምላሽ ለወደፊት ተቃውሞ የበለጠ እንዲባባስ ሊያደርግ እንደሚችል ሂማን ራይትስ ወች ገልጿል።
የኢትዮጵያ መንግስት ጭካኔ የተሞላው የግፍ አያያዝን በተመከተ የተባበሩት መንግስታት የሰብአዊ መብት ምክርቤትን ጨምሮ ሌሎች ጉዳዩ የሚመለከታቸው መንግስታት እና መንግስታዊ ተቋማት ጠንካራና የተቀናጀ ምላሽ የሚጠይቅ ነው በማለት ሂዩማን ራይት ዎች አሳስቧል። የአውሮፓ ህብረት ፓርላማ ድርጊቱን በማውገዝ ጠንከር ያለ የአቋም መግለጫ ያወጣና ይሄው መግለጫም ለአሜሪካ መንግስት የተገለጸ ቢሆንም በኦሮሚያ ክልል የተፈጸመው የግፍ ድርጊት በአለማቀፍ ደረጃ በአብዛናው በዝምታ የታለፈ ነው። የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የሰብአዊ መብቶች ምክርቤት ይህን ከፍተኛ የመብት ጥሰት በአትኩሮት ሊያየው፣ ያለአግባብ ለእስር የተዳረጉት እንዲፈቱና አስቸኳይ ገለልተኛ የሆነ ማጣሪያ እንዲካሄድ ጥሪ ሊያደርግ ይገባል።
"የኢትዮጵያን መንግስት የሚደግፉ አብዛኛዎቹ የውጭ አጋር ተቋማት መንግስት በኦሮሚያ ክልል የወሰደውን አስከፊ አፈና በተመለከተ በዝምታ አልፈውታል፡፡" በማለት ሌፍኮው ተናግሯል። "የኢትዮጵያን ልማት የሚደግፉ ሀገራት በኢትዮጵያ በሁኒም መስኩ መሻሳሎች እንዲታዩ ጫና ማድረግ አለባቸው፤ በተለይም የንግግር ነጻነትና ለተጠቂዎች ፍትህ እንዲያገኙ መስራት ይጠበቅባቸዋል። " ብለዋል።