Skip to main content

የመን፡ በስደተኞች ማጎርያ ቤት ላይ በተነሳ የእሳት ቃጠሎ በርካቶች ስደተኞች ለሞት ተዳረጉ

የተባበሩት መንግስታት የኤክስፐርቶች ቡድን የሁቲ ታጣቂዎች የሚያደርሱትን ጥቃት መመርመር አለባቸው

Read a text description of this video

አብዛኞቹ የኢትዮጵያ ዜጎች የሆኑ እና በስደተኛ ማጎሪያዎች ለረሀብ የተዳረጉ  በየመን፣ ሰነዓ የፓስፖርት እና የዜግነትጉዳይ ባለስልጣን የታገቱ ስደተኞች። የካቲት 28 ቀን 2013 ዓ.ም ስደተኞቹ የታጎሩበት ጣቢያ አሰቃቂ ሁኔታ እና ያለአንዳች ወንጀል (ክስ) መታሰራቸውን በመቃወም የረሀብ አድማ አደረጉ። በዚህ ወቅት የማጎሪያ ጣቢያው ጠባቂዎችከስደተኞቹ ጋር ሰጣ ገባ ውስጥ ከገቡ በኋላ ሁሉንም ስደተኞች በማጎርያ ክፍሎች ካስገቧቸው በኋላ ምግብናመጠጥ ከለከሏቸው። ከዝያም ጠባቂዎቹ ከአካባቢው ለደቂቃዎች ከተሰወሩ በኋላ ሙሉ የጦር መሳርያ የታጠቁየሁቲ የጸጥታ ሀይሎች ጋር ተመልሰው መጡ። ከመካከላቸው አንደኛው የጥበቃ አባል ክፍት ስፍራ ካለው ጣርያውላይ በመውጣት ሁለት ተቀጣጣይ ፈንጂዎችን ስደተኞቹ ወዳሉበት ክፍል ወረወረ። በመጀመርያ የወረወረውከፍተኛ ጪስ በመፍጠር የስደተኞቹ አይኖች በእንባ እንዲሞሉ እና ማየት እንዳይችሉ አደረገ። ሁለተኛ የተወረወረውፈንጂ ደግሞ የእሳት ቃጠሎ አስነሳ። በግምት ከ10 እስከ 15 ደቂቃ ቆይታ በኋላ ከውጭ የነበሩ ሌሎች ሰዎችየስደተኞቹን ክፍሎች ግድግዳና በሮች በማፍረስ የተወሰኑ ስደተኞችን ህይወት ሲያተርፉ በርካቶች ግን በአስከፊሁኔታ ሞተዋል።

(ቤሩት፣ መጋቢት 7 ቀን 2013 ዓ.ም) – በየካቲት 28 ቀን 2013 ዓ.ም በየመኗ ዋና ከተማ ሰነአ ውስጥ በሚገኝ አንድ የስደተኞች ማጎርያ ጣቢያ የሆቲ የጸጥታ ሀይሎች ለጊዜው አይነቱ እና ምንነቱ ተጣርቶ ባልታወቀ ከፍተኛ የጦር መሳርያ በስደተኞች የማጎሪያ ጣቢያው ላይ በከፈቱት ተኩስ የተነሳ የእሳት ቃጠሎ በርካታ ስደተኞች ለሞትና ለከፋ የአካል ጉዳት መዳረጋቸውን ሂዩማን ራይስት ዎች ዛሬ ባወጣው ሪፖርቱ አስታውቋል።

በመቶዎች የሚቆጠሩ እና ከነዚህ መካከል ከፍተኛ ቁጥር ኢትዮጵያውያን የሚገኙበት ስደተኞች የታሰሩበት የስደተኞች ማጎርያ ጣቢያው አስከፊ አያያዝ አስመልክቶ ተቃውሞ ሲያሰሙ የነበሩ ሲሆን በዚሁ ሳቢያ ስደተኞች ጥቃቱ ከደረሰባቸው በኋላ በዋና ከተማዋ ውስጥ በሚገኝ አንድ ሆስፒታል ውስጥ የእሳት አደጋ እርዳታ እየተደረገላቸው ይገኛል። ይሁን እንጂ ሆስፒታሉ ከፍተኛ ቁጥር ባላቸው የጸጥታ ሀይሎች የተከበበ በመሆኑ ተጎጂዎቹ በዘመዶቻቸው እንዲሁም በሰብአዊ መብት ተሟጋች ድርጅቶች እንዳይጎበኙ እና አስፈላጊውን እርዳታ እንዳያገኙ እንቅፋት ፈጥሯል።

አንሳር አላህ በመባል የሚጠራው የሆቲ ታጣቂ ቡድን በአስቸኳይ የስደተኞቹን ማጎርያ ለግብረ ሰናይ ድርጂቶች ክፍት በማድረግ የጤና እንዲሁም ሌሎች አስፈላጊ ድጋፎች ለስደተኞቹ እንዲደረግ መፍቀድ አለበት:: የተባበሩት መንግስታት ድርጂት የመርማሪዎች ቡድን እንዲሁም በየመን አጠቃላይ ጉዳይ ላይ የሚሰሩ የቀጣናው የሰብአዊ መብት ባለሙያዎች በሀገሪቱ ውስጥ እያካሄዱት ባለው የሰብአዊ መብት ጥሰት የማጣራት ሂደት ውስጥ ይህንኑ ጉዳይ ሊያካትቱት ይገባል።

“በዚህ የሁቲ ታጣቂዎች ዝርዝክርክ እና ጥንቃቄ የጎደለው የጦር መሳርያ አያያዝና አጠቃቀም ሳቢያ በርካታ ኢትዮጵያውያን ስደተኞች በአስከፊ የእሳት ቃጠሎ መሞታቸው በጦርነት በወደመችው የመን ውስጥ ስላለው አደገኛና አስቀያሚ የስደተኞች አያያዝ ሁኔታ ዳግም እንድናስብ አድርጎናል” ሲሉ የሂዩማን ራይትስ ዎች የስደተኞችና የስደተኞች መብት ተመራማሪዋ ናዲያ ሃርድማን ገልጸዋል። “የሁቲ ባለስልጣናት በጉዳዩ ላይ እጃቸው ያለበትን በአስቸኳይ ለህግ ማቅረብ አለባቸው። እንዲሁም ስደተኞችን ለህይወታቸው እጅግ አደገኛ በሆነ አስከፊ የማጎርያ ጣቢያዎች ማከማቸት ማቆም አለባቸው” በማለት አሳስበዋል።

በርካታ የኢትዮጵያ ዜጎች የሆኑ ስደተኞች በየመን ሰነዓ የስደተኞች እና የፓስፖርት ጉዳይ ባለስልጣን የስደተኞችማጎርያ ጣቢያ ውስጥ በቀን የካቲት 28/2013 የረሀብ አድማ ያደረጉበት እና በርካታ ኢትዮጵያውያን በእሳትተቃጥለው የሞቱበትን ስፍራ የሚያሳይ ምስል። በማክሰር ቴክኖሎጂስ በቀን እ.ኤ.አ ኖቬምበር 7/2020 የተነሳየሳተላይት ምስል። ምንጭ፡ ጉግል ኤርዝ፣ © 2021 ሂዩማን ራይትስ ዎች በማክሰር ቴክኖሎጂስ በቀን እ.ኤ.አ ኖቬምበር 7/2020 የተነሳየሳተላይት ምስል። ምንጭ፡ ጉግል ኤርዝ፣ © 2021 ሂዩማን ራይትስ ዎች

የሁቲ ታጣቂ ቡድን ጥቃት የደረሰበትን የስደተኞች ማጎሪያ ጣቢያ የሚገኝባትን እና የየመን ዋና ከተማ ሰነአን ጨምሮ አብዛኛውን የሀገሪቱን ክፍል ይቆጣጠራል። አለማቀፉ የስደተኞች እንዳወጣው መረጃ ከሆነ ከስድስት ሺህ (6000) በላይ ስደተኞች በየመን የተለያዩ ማጎርያዎች ውስጥ ይገኛሉ። ህገ ወጥ የስደተና አዟዟሪዎች ደግሞ በመቶና በሺህ የሚቆጠሩትን በተመሳሳይ መልኩ ይዘዋቸዋል።

ሂዩማን ራይትስ ዎች በስደተኞቹ ማጎሪያ ከሚገኙ አምስት ኢትዮጵያውያን ስደተኞች ጋር በስልክ ያነጋገረ ሲሆን የየመን የስደተኞች የፓስፖርትና የዜግነት ባለስልጣን መስርያ ቤትን (IPNA) እንዲሁም በየመን የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ተወካዮችን በጉዳዩ ላይ አነጋግሯል።

በሂዩማን ራይስት ዎች ቃለ መጠይቅ የተደረጉት ስደተኞች እንደሚናገሩት ከሆነ የማጎርያ ክፍሎቹ እጅግ በጣም የተጣበቡና ንጽህናቸው በአግባቡ ያልተጠበቀ ነው፡፡ ክፍሎቹ እስከ 550 ስደተኞች ተጨናንቀው የታጎሩበት ሲሆን ስደተኞቹ በረሀብ እየተሰቃዩ ይገኛሉ ብለዋል፡፡ የመተኛ ፍራሽ የማይሰጣቸው ሲሆን ከማጎሪያ ቤቱ ጠባቂዎች ፍራሾችን እንደሚገዙ ነው ስደተኞቹ የተናገሩት፡፡ የምግብ እጥረት ያለባቸው ሲሆን ንጹህ የመጠጥ ውሀም እንደሌላቸውና የመጸዳጃ ቤቶችን የመታጠቢያ ውሀ ለመጠጣት እንደሚገደዱ ገልጸዋል፡፡

ለበርካታ ሳምንታት በተጨናነቀው የማጎርያ ክፍሎች ውስጥ ለመኖር የተገደዱት ስደተኞች ይህንኑ የስቃይ አያያዝ በመቃወም እና ለረዥም ጊዜ በዚህ ሁኔታ መያዛቸውን በመቃወም የረሀብ አድማ ለማድረግ አቅደው እንደነበረ ተናግረዋል፡፡ ስደተኞቹ እንደሚናገሩት ከታማጎርያው ጣቢያ ለመለቀቅ ከፈለጉ 70 የየመን ሪያል (280 ዶላር) ለጥበቃዎቹ ለመክፈል ይገደዳሉ፡፡ ከዚህም ባሻገር ከፍተኛ የመብት ጥሰት እንደሚፈጸምባቸውና አስጸያፊና የዘረኝነት ስድቦችን እንደሚሰደቡ እንዲሁም ማስፈራርያ እንደሚደርስባቸው ስደተኞቹ ተናግረዋል፡፡

እንደ ስደተኞቹ ማብራርያ ከሆነ መጋቢት 28 ቀን ጠዋት ስደተኞቹ ምግብ ላለመብላት ወሰኑ፡፡ ከቀኑ ሰባት ሰዐት አካባቢ የጥበቃው ሰራተኛ ምሳ ይዞ ቢመጣም አሁንም ስደተኞቹ እንደማይበሉ ገለጹ፡፡ ጥበቃዎቹም በድንገት በመምጣት የረሀብ አድማ አስተባባሪዎቹን ለይተው ወደ ውጭ በመውሰድ በዱላና በጠመንጃ ሰደፍ ደበደቧቸው ብለዋል ስደተኞቹ፡፡ በዚህ የተበሳጩት ስደተኞቹም የመመገቢያ ሳህኖችን በመወርወር አንድ የጥበቃ ሰራተኛ ፊቱ ላይ ጉዳት አድርሰዋል፡፡ ከዝያ በኋላ የጥበቃ ሰራተኞቹ ስደተኞቹን በመክበብ እንዳይንቀሳቀሱ በማድረግ እንዲራቡ አደረጓቸው፡፡

የጥበቃ አባላቱ አካባቢውን ለቀው ሄደው ከጥቂት ደቂቃዎች በኋላ ጥቁር፣ አረንጓዴና ግራጫ ዩኒፎርም ከለበሱ ወታደሮች ጋር ሆነው ተመልሰው መጡ፡፡ ሲመለሱ የተሟላ የጦር መሳርያ ጠመንጃ ታጥቀው ነበር፡፡ “ከተመለሱ በኋላ የመጨረሻውን ጸሎታችንን ወደ ፈጣሪ እንድናደርግ አዘዙን” ሲሉ ይናገራሉ ስደተኞቹ፡፡

አዲስ ከመጡት ወታደሮች መካከል አንደኛው ክፍት ቦታ ወዳለው ከጥበቃው ማማ ላይ በመውጣት ሁለት ፈንጂዎችን ወደ ስደተኞቹ ማጎርያ ክፍል ወረወረ፡፡ እንደ ስደተኞቹ ገለጻ በመጀመርያ የወረወረው ፈንጂ ከፍተኛ ጭስ የፈጠረ ሲሆን አይናቸውን የሚያቃጥልና እምባ የሚያስመጣ ነው፡፡ ሁለተኛው ደግሞ ቦንብ እንደሆነና ይህም የፈጠረው እሳት ቃጠሎውን እንዳስነሳ ስደተኞቹ ተናግረዋል፡፡ ይሁን እንጂ ሂዩማን ራይትስ ዎች የተወረወሩት ሁለት ፈንጅዎች አይነታቸውን ለመለየት ያልቻለ ቢሆንም ከአይን እማኞች ገለጻ ለመረዳት እንደተቻለው የመጀመርያው ፈንጂ አስለቃሽ ጋዝ፣ የጭስ ጋዝ፣ ስቱን ጋዝ ወይም ፍላሽ ጋዝ ሊሆን እንደሚችል ይገመታል፡፡

አንድ የ20 አመት እድሜ ያለው ስደተኛ “ከፍተኛ ጭስ እና ከባድ እሳት ነበር” ሲል ተናግሯል። “በወቅቱ የነበረውን ሁኔታ ለመግለጽ የሚሆን ቃላት የለኝም። የተወረወረው ፈንጂ ሲፈነዳ አካባቢው በከፍተኛ ጪስ ተሞላ። ከዝያም እሳት ተቀጣጠለ። በጣም አስደንጋጭና አስፈሪ ነበር። እኔ አዕምሮዬ በጭሱ ብዛት የተዘጋ መስሎ ነበር የተሰማኝ። በዙርያዬ የነበሩ ሰዎች በሙሉ ያስላሉ። ፍራሾቹና ብርድ ልብሶቹ በእሳት መያያዝ ጀመሩ። ሰዎች ከነ ነፍሳቸው ተቀቀሉ። እኔ በሟቾች ሬሳ ላይ እየተረማመድኩ ራሴን ለማትረፍ ማምለጥ ነበረብኝ።”

“ከአስር እስከ አስራ አምስት ደቂቃዎች በኋላ ሰዎች ከውጭ የክፍሎቹን ግድግዳዎችና በሮች በመስበር ከፈቱልንና ከፍንዳታው የተረፍነውን በአቅራቢያው ወዳለ ሆስፒታል ወሰዱን።

ሂዩማን ራይትስ ዎች በወቅቱ የተቀረጹ ሁለት የቪዲዮ መረጃዎች እንዲሁም የእሳት ቃጠሎ አደጋው ከተፈጸመ በኋላ ራሳቸውን ለማዳን በመጣር ላይ የነበሩና በእሳቱ ተቃጥለው የሞቱ በርካታ የሰዎች አስከሬን በየቦታው ወዳድቀው የቪዲዮ ምስል የደረሰው ሲሆን እነዚህን የተለያዩ ቪዲዮዎች በመመርመር የአይን እማኙ ከሰጠው ምስክርነት ጋር ተመሳሳይ መሆናቸውን ለማረጋገጥ ተችሏል።

ይህ ከሆነ በኋላ በአደጋው ጉዳት ደርሶባቸው የሚታከሙበት ሆስፒታል ከፍተኛ ቁጥር ባላቸው የጸጥታ ሀይሎች ተከቦ ጥበቃ ይደረግበት ጀመር። ቃለ መጠይቅ የተደረገላቸው እንደተናገሩት የሁቲ የጸጥታ ሀይሎች ከአደጋው የተረፉትን እና እምብዛም ጉዳት ያልደረሰባቸውን ፍልሰተኞች በቁጥጥርስ ስር ሲያውሏቸው መመልከታቸውን ተናግረዋል።

አለማቀፉ የስደተኞች ድርጅት (IOM) ሁቲዎች በሆስፒታሉ ውስጥ የእርዳታ ሰራተኞችና የጤና ባለሙያዎች እንዲገቡ መፍቀድ አለባቸው ብሏል።

የካቲት 28 ቀን 2013 ዓ.ም የሁቲ የሀገር ውስጥ ጉዳይ ሚኒስትር ባወጣው መግለጫ አለማቀፉ የስደተኞች ድርጂት (IOM) እና የተባበሩት መንግስታት ድርጂት (UN) ለፍልሰተኞቹ መጠለያ ማዘጋጀት ባለ መቻላቸው በተፈጠረው ጉዳት ተጠያቂ ናቸው ብሏል።

ከሂዩማን ራይትስ ዎች ጋር የተነጋገሩት የሆቲ የህዝብ ግንኙነት ሀላፊ አቶ መሀመድ አብዱሰላም “የተፈጠረው አደጋ የትም አለም ላይ በማንኛውም ጊዜ ሊደርስ የሚችል የተለመደ ክስተት ነው” ብለዋል። “በመሆኑም ይህን ጉዳይ ፖለቲካዊ ማድረግ እንዲሁም ከክስተቱ ውጪ የሆነ ትርጓሜ መስጠት አስፈላጊ አይደለም። በዚህ ጉዳይ ላይ ትኩረት ማድረግ አስፈላጊ ሆኖ ከተገኘም በሀገሪቱ ውስጥ የሚገኙ የህገ ወጥ ስደተኞችን ችግር መፍታት እና ሁኔታውን ማሻሻል ያለባቸው እነዚህ አለማቀፍ ተቋማት ላይ ትኩረት መደረግ አለበት። እነዚህ ተቋማት የስደተኞች ማጎርያ (ማቆያዎችን) እንዲያሻሽሉ እንዲሁም የሰንአ አየር ማረፊያ አገል ግሎት መስጠት እንዲጀምርና ስደተኞቹ ወደ ሀገራቸው እንዲመለሱ እንዲደረግ ግፊት ማድረግ አለባቸው። እነዚህን መሰረታዊ ነገሮች ሳያደርጉ ወደ አላስፈላጊ ነገሮች ውስጥ መግባት ችግሩን ሊፈታው አይችልም።” በማለት አቶ መሀመድ አብራርተዋል።

“ስለ እውነት ለመናገር የሰነዐ ባለስልጣናት ከህገ ወጥ ስደተኞቹ ጋር የፖለቲካም ሆነ የማንኛውም አይነት ግጭት ነክ ችግር ፈጽሞ የለባቸውም። በመሆኑም የሰነዓ ባለስልጣናት በደረሰው አደጋ ዙርያ መግለጫ አውጥተዋል። ከዚህም በተጫማሪ ጉዳት የደረሰባቸው ህገ ወጥ ስደተኞች ሀገራት ኤምባሲዎችም በጉዳዩ ዙርያ ማብራርያ እንዲሰጣቸው እና የአደጋው መንስኤ ምን እንደሆነ እንዲገለጽላቸው ጠይቀዋል።”

ስደተኞቹ የኮቪድ-19 ቫይረስ ተሸካሚዎችና አስተላላፊዎች ናቸው በሚል በመፈረጃቸው ሳቢያ በሁቲዎች ቁጥጥር ስር በሆነችው እንዲሁም አለማቀፉ ደረጃ እውቅና የተሰጠው የየመን ሰሜናዊ ግዛት ስደተኞቹ በግዳጅ እየተላለፉ እንደሚሰጡ የአለማቀፉ የስደተኞች ድርጂት (IOM) ማረጋገጡን አስታውቋል።  እንደ አውሮፓውያኑ አቆጣጠር በ2020 ዓ.ም ከ15 ሺህ በላይ ስደተኞች ከሰሜናዊው የሀገሪቱ ክፍል ወደ ደቡብባዊው የሀገሪቱ ክፍል በግዳጅ ተሰጥተዋል። ቃለ መጠይቅ የተደረገላቸው ስደተኞች ከእሳት አደጋው የተረፉ በርካታ ስደተኞች ወደ ደቡባዊው የየመን ግዛት ተላልፈው እንደተሰጡ እርግጠኞች መሆናቸውን ተናግረዋል።

ሂዩማን ራይስት ዎች በሚያዝያ ወር 2013 ዓ.ም ባወጣው ሪፖርት የሁቲ ታጣቂ ሀይሎች በሺህ የሚቆጠሩ ኢትዮጵያውያን ስደተኞችን ከሰሜናዊ የየመን ግዛት አካባቢዎች የኮረና ቫይረስን እንደ ቅድመ ሁኔታ በማስቀመጥ በሀይል እንዳስወጧቸው፣ በርካቶችንም እንደገደሏቸው እንዲሁም ከሳውዲ አረቢያ ጋር ጥምረት በመፍጠር ስደተኞችን በድንበር አካባቢዎች ከፍተኛ ችግር እንደፈጠሩባቸው መግለጹ ይታወቃል።

ከዚህም በተጨማሪ ሂዩማን ራይትስ ዎች በችግር የተሞላውን  ከአፍሪካ ቀንድ ወደ የመን እና ሳውዲ አረቢያ የሚያደርጉትን የስደተኞች ጉዞና በዚህም በየመን ግጭት ውስጥ ተሳታፊ የሆኑ አካላት ሳይቀር የሚደርስባቸውን እንግልት በዝርዝር ዘግቧል።

እ.ኤ.አ በ2018 ሂዩማን ራይትስ ዎች ባወጣው ሪፖርት የየመን መንግስት ባለስልጣናት ኤደን ውስጥ በሚገኝ የስደተኞች ማጎሪያ ጣቢያ ውስጥ ከአፍሪካ ቀንድ የመጡ ስደተኞችን ማሰቃየታቸውንና የጾታ ጥቃት እንዳደረሱባቸው እና እንደገደሏቸው ይፋ አድርጓል። በተጨማሪም እ.ኤ.አ በ1019 ሂዩማን ራይትስ ዎች ባወጣው ዘገባ ህገ ወጥ ደላሎች፣ ስደተኛ አመላላሾች፣ እና የየመን ባለስልጣናት በፈጠሩት የጥምረት ኔትወርክ ኢትዮጵያውያንን ስደተኞች እንደሚያፍኑ፣ እንደሚያስሩ እና ድብደባ እንደሚፈጽሙባቸው ለሽያጭ እንደሚያቀርቧቸው አልያም ቤተሰቦቻቸው ገንዘብ እንዲከፍሉ እንደሚያደርጉ ዘግቧል።

የሁቲ ባለልጣናት ስደተኞችን በእስር ማቆየት ያለባቸው በተለየ ሁኔታ አስፈላጊ ሲሆንና እንዲሁም የስደተኞቹ የእስር ጣቢያ ከአለማቀፍ ህጎችና የተባበሩት መንግስታት ድርጂት ህጎችን ያሟሉ ሲሆን ብቻ መሆኑን ሊገነዘቡ ይገባል። (የማንዴላ ህጎች)

እያንዳንዱ እስረኛ በ48 ሰአታት ውስጥ በዳኛና በፍርድ ቤት ቀርቦ የታሰረበት ምክኒያት እና የእስሩ ህጋዊነት እና አስፈላጊነት ሊጣራ ይገባል። በህጉ መሰረት ታሳሪዎቹ መለቀቅ አለባቸው አልያም ያሰሯቸው ባለስልጣናት ህጋዊ ማስረጃና መረጃ በእያንዳንዱ ታሳሪ ላይ ሊያቀርቡ እና ታሳሪዎቹም በዚሁ መሰረት ሊመረመሩ አልያም በህጋዊ መንገድ ወደ ሀገራቸው ሊመለሱ ይገባል።

የሁቲ ባለስልጣናት በአስቸኳይ በየመን ውስጥ ጉዳት የደረሰባቸውንና የጠፉበት ያልታወቁ ዜጎቻቸውን አስመልክቶ በስደተኞች ማጎርያው ዙርያ የኢትዮጵያ ባለስልጣናትን በማካተት ማጣራት ሊያደርጉ ይገባል።  አለማቀፉ የስደተኞች ድርጂት (IOM) ስደተኞቹን ከየመን በፈቃደኝነት ወደ ሀገራቸው እንዲመልስ ሊፈቀድለት ይገባል። የተባበሩት መንግስታት የስደተኞች ጉዳይ ኮሚሺን (UNHCR) አካባቢው ሙሉ በሙሉ ክፍት እንዲሆንለት እና የስደተኝነት ጥያቄ የሚያቀርቡትን ሁኔታቸውን እንዲያጣራ ሊደረግ ይገባል። ከዚህም ባሻገር ወደ ሀገራቸው ለመመለስ ፈቃደኛ የሆኑትን ለመመለስ የተባበሩት መንግስታት በሰብአዊ መብት ኤጀንሲዎች በኩል የሚደረግና ሙሉ በሙሉ በፈቃደኝነት ላይ የተመሰረተ መሆን አለበት። እንዲሁም ለጋሾች የተመላሾችን የጤናና የስነልቦና ድጋፍ በማድረግ ወደ ኢትዮጵያ እንዲመለሱና ከቤተሰቦቻቸው ጋር እንዲቀላቀሉ ማድረግ ይኖርባቸዋል።

“ለጋሽ ሀገራትም እነዚህ በገልፍ የስደተኞች የጉዞ መስመር ላይ ከፍተኛ እንግልት የደረሰባቸውን ስደተኞች እና በአይምሮ ለማሰብ የሚከብድ ስቃይ የተቀበሉትን ወደ ሀገራቸው ለመመለስ ይቻል ዘንድ አስፈላጊውን እርዳታና ድጋፍ ሊያደርጉ ይገባል” ሲሉ ሃርድማን ተናግረዋል።

Your tax deductible gift can help stop human rights violations and save lives around the world.

Region / Country