በኢትዮጵያ ያለው የሰብኣዊ መብት ሁኔታ ኣሳሳቢ ሆኖ ቀጥሏል። በመንግስት የጸጥታ ሃይሎች፣ ሚሊሻዎች እና መንግስታዊ ያልሆኑ ታጣቂ ቡድኖች ለሚፈፀሙ ስልታዊ ጥቃቶች ተገቢ ተጠያቂነትና ቅጣት ኣለመኖር እንደተለመደው ቀጥሏል።
በነሓሴ ወር በኣማራ ክልል ታጣቂዎች እና በኢትዮጵያ መከላከያ መካከል የነበረው ግጭት ተባብሶ በመቶዎች ለሚቆጠሩ ዜጎች ሞትና የኣካል ጉዳት፣ የሲቪል መሰረተ ልማቶች ውድመት እና መፈናቀል ምክንያት ሆኗል። ለዚህ ምላሽ የፌደራል መንግስት ለክልሉ ሰፊ የኣስቸኳይ ጊዜ ኣዋጅ ቢያወጣም በተግባር ግን ድንጋጌዎቹ በመላ ሀገሪቱ ተግባራዊ ሆነዋል።
እ.ኤ.ኣ በጥቅምት 2022 በፌዴራል መንግስት እና በትግራይ ባለስልጣናት መካከል ከተደረገው ጠብን የማቆም ስምምነት በኋላ በሰሜን ኢትዮጵያ ግጭት ውስጥ የተሳተፉት ሁለቱ ዋና ተዋጊ ወገኖች በትግራይ ክልል ያደርጉ የነበረው ውጊያ ኣብቅቷል። ሆኖም በትግራይ ሰላማዊ ዜጎች ላይ ከፍተኛ የመብት ረገጣ ዓመቱን ሙሉ ቀጥሏል፤ በተለይም በምዕራብ፣ ሰሜን ምዕራብ እና ምስራቃዊ ትግራይ ዞኖች።
እስከ መስከረም ወር ድረስ በኢትዮጵያ በግጭት ምክንያት 2.9 ሚሊዮን የተፈናቀሉ ሲሆን ከ141,000 በላይ ኢትዮጵያውያን ስደተኞች እና ጥገኝነት ጠያቂዎች በጎረቤት ሀገራት እንዳሉ የተባበሩት መንግስታት የስደተኞች ኤጀንሲ ዩ. ኤን. ኤች. ሲ. ኣር. ኣስታውቋል።
ጋዜጠኞች፣ የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች እና ታዋቂ ግለሰቦች ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ የሚገኝ የጥላቻ እና ለዘጋቢነት የማይመችና ገዳቢ ሁኔታ ገጥሟቸዋል።
በኢትዮጵያ የሚገኙ የተመሳሳይ ፆታ፣ ሁልትዮሽ ፆታ እና ተሻጋሪ ፆታ አፍቃሪ ሰዎች የኢንተርኔት ላይ ትንኮሳ እና ኣካላዊ ጥቃት ደርሶባቸዋል። የኣዲስ ኣበባ ሰላምና ፀጥታ ኣስተዳደር ቢሮ ከፍተኛ የኦንላይን ዘገባ መሰራቱን ተከትሎ “የግብረ ሰዶም ድርጊቶች በሚፈጸሙባቸው ተቋማት” እንደ ሆቴሎች እና ሌሎች የንግድ ተቋማት ላይ እርምጃ እየወሰደ መሆኑን ገልጿል። በስምምነት ላይ የተመሠረቱ የተመሳሳይ ጾታ ግንኙነቶች በህግ የተከለከሉ ሲሆኑ እስከ 15 ኣመት እስራት ያስቀጣሉ።
መንግስት በሰሜን ኢትዮጵያ በተከሰተው ግጭት ወቅት የተፈፀሙትን ግፍ ጨምሮ ባለፉ እንዲሁም በቀጣይነት እየተፈፀሙ በሚገኙ በደሎች ለተፈፀመው ግፍና በደል ተጠያቂነትን ለማስፈን የሚያደርገው ጥረት በቂ ያልሆነ፣ ግልጽነት የጎደለው እና ገለልተኛ ቁጥጥር ያልተደረገበት ነው።
የሰሜናዊ ኢትዮጵያ ግጭት
እ.ኤ.ኣ ከህዳር 2022 ፀብን የማቆም ስምምነት ከተደረገ ወዲህ በትግራይ የሰብኣዊ መብት ረገጣ ቀጥሏል።
የፀብ ማቆም ስምምነቱ ከተደረገ ከወራት በኋላ በትግራይ የሚገኙ የኤርትራ ወታደሮች በተቆጣጠሩት ኣካባቢ በሚገኙ የትግራይ ሴቶች እና ልጃገረዶች ላይ ፆታዊ ባርነትን ጨምሮ የኣስገድዶ መድፈርና ፆታዊ ጥቃት ኣድርሰዋል፤ ህጋዊ ያልሆኑ ግድያዎችንና ኣፈናዎችን ፈፅመዋል፤ ኣንዲሁም የዜጎችን ንብረት ዘርፈዋል። በግንቦት ወር የኤርትራ ሃይሎች የኣስገድዶ መድፈር፣ የዘረፋ እና የንብረት ማውደም በቀጠሉባቸው ሁለት መንደሮች የሰብኣዊ ተልእኮ እንዳይገባ ኣግደዋል ። በዚያው ወር የኤርትራ ይሎች የእርቁን ትግበራ ለመከታተል የተቋቋመውን የኣፍሪካ ህብረት ክትትል፣ ማረጋገጫ እና ተገዢነት ሜካኒዝም (AU-MVCM) ስራውን እንዳደናቀፉ ተዘግቧል።
በምዕራብ ትግራይ ዞን የኣካባቢው ባለስልጣናት፣ የኣማራ ክልል ሃይሎች እና “ፋኖ” በሚል ስም የሚታወቁ ታጣቂዎች እ.ኤ.ኣ በሕዳር 2022 እና በጥር 2023 በትግራይ ተወላጆች የዘር ማፅዳት ዘመቻና በግዳጅ ማፈናቀላቸውን የቀጠ ሉ ሲሆን የትግራይ ተወላጆች መታሰር እና ከዞኑ የማፈናቀል ዘገባዎች እስከ ነሓሴ ድረስ ቀጥለዋል።
በመጋቢት ወር የተባበሩት መንግስታት የኣለም ምግብ ፕሮግራም (WFP) እና የዩናይትድ ስቴትስ ኣለም ኣቀፍ የልማት ኤጀንሲ (USAID) “የእርዳታ እህል በኣገር ውስጥ ገበያ እየተሸጠ ነው” የሚሉ ሪፖርቶች ከወጡ በኋላ ለትግራይ የሚሰጠውን የምግብ እርዳታ ኣቆሙ። ኤጀንሲዎቹ ባደረጉት ምርመራ በፌደራል እና በክልል የመንግስት ኣካላት የምግብ እርዳታን ወደ ሌላ ኣቅጣጫ ለመቀየር “የተስፋፋ እና የተቀናጀ እቅድ” በማግኘታቸው በሰኔ ወር እገዳውን ወደ መላ ኢትዮጵያ ኣሰፉት።
እ.ኤ.ኣ በሰኔ ወር ወደ 20 ሚሊዮን ሰዎች የሚገመቱ የምግብ እርዳታ ለሚያስፈልጋቸው ሰዎች የምግብ ኣቅርቦትን በከፍተኛ ሁኔታ በመገደቡ በተለይ በተፈናቃዮች እና በስደተኛ ካምፖች ውስጥ ባሉ ሰዎች ከረሃብ ጋር የተያያዙ የሞት ዘገባዎች ጨምረዋል። በጥቅምት ወር የኣለም ምግብ ፕሮግራም እና የዩናይትድ ስቴትስ ኣለም ኣቀፍ የልማት ኤጀንሲ የምግብ ዕርዳታውን ለስደተኞች መስጠት የቀጠሉ ሲሆን ለሌሎች የምግብ ዋስትና የሌላቸው ህዝቦች የሚሰጠው ዕርዳታ እንደተቋረጠ ነው።
በደህንነት ሃይሎች የሚፈፀሙ በደሎች፡ በታጠቁ ቡድኖች የሚሰነዘሩ ጥቃቶች
የፌደራል መንግስት የክልሉን የፖሊስ ሃይል ወደ ፌደራል ወታደራዊ ሃይል ለማዋሃድ መወሰኑን ተከትሎ በሚያዝያ ወር የኣማራ ክልል የጸጥታ ሁኔታ እየተባባሰ መጣ። እ.ኤ.ኣ በሚያዝያ 9 ሁለት የካቶሊክ የእርዳታ ኣገልግሎት ኣባላት በጥይት ተመተው ተገድለዋል።
በነሓሴ እና መስከረም ወራት በኣማራ ክልል በሚገኙ ከተሞችና ዙርያዎቻቸዉ በሚገኙ ኣካባቢዎች ከባድ ጦርነት መከሰቱ ተዘግቧል። በዚህም ህጻናትና ስደተኞችን ጨምሮ በመቶዎች የሚቆጠሩ ተገድለዋል እና ቆስለዋል፤ እንዲሁም በሲቪል ንብረት እና እንደ ሆስፒታሎች ያሉ መሰረተ ልማቶች ላይ ውድመት ደርሷል። እ.ኤ.ኣ ነሓሴ 29 የተባበሩት መንግስታት የሰብኣዊ መብቶች ከፍተኛ ኮሚሽነር (OHCHR) ፅህፈት ቤት ከሓምሌ ወር ጀምሮ በተካሄደው ጦርነት ቢያንስ 183 ሰዎች መሞታቸውን ኣረጋግጧል።በኣማራ ክልል በመንግስት የጸጥታ ሃይሎች በተደረጉ የቤት ለቤት ፍተሻዎች ግለሰቦች በቁጥጥር ስር ውለዋል።
እ.ኤ.ኣ ነሓሴ 5 የኢትዮጵያ ፓርላማ በኣማራ ክልል ኣስፈላጊ ሆኖ ከተገኘ ወደ የትኛውም የሀገሪቱ ክፍል ሊቀጠል የሚችል ሰፊ ተፈፃሚነት ያለዉ የኣስቸኳይ ጊዜ ኣዋጅ ኣውጥቷል። የኣስቸኳይ ጊዜ ኣዋጁ የወንጀል ተጠርጣሪዎችን ያለፍርድ ቤት ትዕዛዝ በቁጥጥር ስር የማዋል፤ የሰዓት እላፊ ገደብ የመጣል፤ የህዝብ ስብሰባዎችን የመከልከል እና ያለፍርድ ቤት ትእዛዝ ፍተሻ የማድረግ ከፍተኛ ስልጣን ለመንግስት ይሰጣል።
በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን መካከል የተፈጠረውን መከፋፈል ተከትሎ በየካቲት ወር በኦሮሚያ ክልል ሻሸመኔ ከተማ ተቃዋሚዎች በተሰበሰቡበት ወቅት ለተቀሰቀሰዉ አመፅ በመንግሥት የጸጥታ ኃይሎች የተሰጠው ምላሽ ግድያና እስራትን ኣስከትሏል።
በሚያዝያ ወር የተካሄደው የሰላም ድርድር ከፈረሰ በኋላ መንግስት በግንቦት ወር በኦሮሞ ነጻነት ሰራዊት (OLA) ላይ የፀረ ሽምቅ ዘመቻውን ዳግም ጀምሯል። በኦሮሚያ ክልል በኦሮሞ እና በኣማራ ማህበረሰቦች ላይ የሚደርሰው ጥቃት እስከ ነሓሴ መጨረሻ ድረስ መቀጠሉ ተዘግቧል። የዓለም ኣቀፍ ቀይ መስቀል ኮሚቴ (ICRC) በሰኔ ወር እንደገለፀው ውጊያው የጤና እንክብካቤ ማእከላትን እና የውሃ ስርዓቶችን ጨምሮ ወሳኝ መሠረተ ልማቶች ላይ ጉዳት አድርሷል።
በመጋቢት ወር የኦሮሚያ ባለስልጣናት በኢትዮጵያ መዲና ኣዲስ ኣበባ ኣቅራቢያ በቅርቡ የተመሰረተችው ሸገር ከተማ የሚገኙ ቤቶችን እና የንግድ ቤቶችን በማፍረስ በቦታው የሚኖሩ በርካታ ነዋሪዎችን ቤት ኣልባ ኣድርገዋቸዋል። የማፍረስ ሂደቱን የተቃወሙ ግለሰቦች በጸጥታ ሃይሎች ድብደባ እና የተኩስ ጥቃት እንደደረሰባቸው ተነግሯል።
በመስከረም ወር በኢትዮጵያ ሶማሌ ክልል በቆሎጂ የተፈናቀሉ የሶማሌ ዜጎች ካምፕ ከኦሮሚያ እና ከሶማሌ ክልል የጸጥታ ሃይሎች ጋር በተያያዘ በተነሳ ግጭት ህይወታቸው ኣልፏል።
የሃሳብ ነጻነት፣ የሚዲያ እና የመደራጀት ነፃነት
የፌደራል መንግስት በወሳኝ ጉዳዮች ላይ የመዘገብ አዉድ ላይ ጥብቅ ቁጥጥር በማድረጋቸው ምክንያት በሀገሪቱ ያለው የሲቪክ ምህዳር መሸርሸሩ ቀጥሏል።
የመንግስት ባለስልጣናት ጋዜጠኞችን፣ ተቃዋሚዎችን እና የሲቪል ማህበረሰብ ተሟጋቾችን በማዋከብ እና በማሰር ወሳኝ ድምጾችን በግድ እያፈኑ ወይም እንዲሰደዱ እያደረጉ ነው።
እ.ኤ.ኣ ጥር 5 ቀን ከኣዲስ ኣበባ ውጪ የግዳጅ መፈናቀልን የሚመለከቱ ጉዳዮችን ሲመረምሩ የነበሩ ዳንኤል ተስፋዬ፣ ብዙኣየሁ ወንድሙ፣ በረከት ዳንኤል እና ሾፌራቸው ናሆም ሁሴን የተባሉ አራት የኢትዮጵያ ሰብኣዊ መብት ጉባኤ (ኢሰመጉ) ሰራተኞችን የኢትዮጵያ ፖሊስ በቁጥጥር ስር በማዋል ለበርካታ ሰዓታት ኣድራሻቸው ሳይታወቅ እንዲሰወሩ አድርገዋል ። እ.ኤ.ኣ ጥር 12 ቀን የኦሮሚያ ፍርድ ቤት ኣራቱን ሰራተኞች በዋስ እንዲለቀቁ ኣድርጓል።
ከነሃሴው የኣስቸኳይ ጊዜ ኣዋጅ ጀምሮ በአማራ ክልል እና በኣዲስ ኣበባ የሚገኙ የኣማራ ተወላጆች ላይ የጅምላ እስራት እየተፈፀመ መሆኑ ተዘግቧል ። በነሓሴ ወር መጀመሪያ ላይ የፌደራል ፖሊስ የተቃዋሚ ፓርላማ ኣባል እና በኣማራ ክልል ገዥውን ፓርቲ እና የመንግስትን ተግባር የሚተቹ ኣቶ ክርስቲያን ታደለ፤ የኣማራ ክልል ምክር ቤት ኣባል የሆኑትን ኣቶ ዮሐንስ ቧያሌውን እና የኣዲስ ኣበባ ከተማ ምክር ቤት ኣባል የሆኑት ኣቶ ካሳ ተሻገርን በቁጥጥር ስር ኣውለዋል። ክርስትያን ታደለ እና ካሳ ተሻገር መጀመሪያ ላይ በድብቅ ቦታ ነበር የታሰሩት።
የኢትዮጵያ ባለስልጣናት እ.ኤ.ኣ ከሚያዝያ 3 እስከ 18 ባለው ጊዜ ውስጥ በኣማራ ክልል ያለው ሁኔታ እየተባባሰ መሄዱን የዘገቡ ስምንት ጋዜጠኞችን በቁጥጥር ስር ኣውለዋል ። ባለስልጣናቱ በነሓሴ ወር የኣስቸኳይ ጊዜ ኣዋጁን ተከትሎ ተጨማሪ ሶስት ጋዜጠኞችን ኣስረዋል ። በመስከረም ወር መጀመሪያ ላይ የኢትዮጵያ ሰብኣዊ መብት ኮሚሽን በኣፋር ክልል በኣዋሽ ኣርባ ወታደራዊ ካምፕ የሚገኙ እስረኞችን ጎበኘ። ከታሰሩት መካከል እንደ ክርስቲያን ታደለ፣ ካሳ ተሻገር፣ እና ስንታየሁ ቸኮል የተባሉ የፖለቲካ ሰዎች እና እንደ ኣባይ ዘውዱ ያሉ ጋዜጠኞች ይገኙበታል።
በመስከረም ወር በህዝባዊ ወያነ ሓርነት ትግራይ (ህወሓት) የሚመራው ጊዜያዊ መስተዳደርን በመቃወም ሰልፍ ለማድረግ ጠይቀው የሰላማዊ ሰልፉ በባለስልጣናቱ ፈቃድ ባለማግኘቱ በትግራይ ክልል ፖሊስ ለሰልፍ የወጡ የተቃዋሚ ፓርቲ ኣመራሮችንና እና ደጋፊዎችን ደብድበዋል፣ አስረዋል ።
የፌደራል መንግስት በተደጋጋሚ የኢንተርኔት እና የማህበራዊ ሚዲያን ተደራሽነት ገድቧል። በትግራይ ክልል ለዓመታት ከዘለቀው የኢንተርኔት ኣገልግሎት መቋረጥ በኋላ የስልክ እና የኢንተርኔት ኣገልግሎት ቀስ በቀስ እንደገና እንዲቀጥል ተደርጓል።
በየካቲት ወር መጀመሪያ ላይ በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ውስጥ የተፈጠረውን ውጥረት ተከትሎ በኦሮሚያ ክልል ሕዝባዊ ተቃውሞ ከተቀሰቀሰ በኋላ ባለሥልጣናት የማኅበራዊ ሚዲያ መድረኮችን ገድበው ነበር። በኣማራ ክልል ጦርነቱ መባባሱን ተከትሎ ባለስልጣናቱ የሞባይል ኢንተርኔት ቢያንስ ሁለት ጊዜ ኣቋርጠዋል።
ተገቢ ሂደት እና የፍትሃዊ ፍርድ መብቶች
የኢትዮጵያ የፌደራል እና የክልል ባለስልጣናት መንግሰትን የሚተቹና የተቃዋሚዎች አመራሮችን በሚመለከቱ የዳኝነት ሂደቶች ላይ የምርመራ ባለስልጣኖች ላይ ጫና በመፍጠር በመደበኛነት ይግባኝ በማለት ወይም የፍርድ ቤት ውሳኔዎችን ችላ በማለት የዳኝነት ሂደቶች ላይ ጣልቃገብነት ኣሳይተዋል።
እ.ኤ.ኣ ከ2020 ጀምሮ በእስር የሚገኙ ሰባት የኦሮሞ ነጻነት ግንባር ታዋቂ ፖለቲከኖች የፍርድ ቤት ትዕዛዝ ከእስር እንዲፈቱ ቢወስንም የኢትዮጵያ ባለስልጣናት እነዚህን ግለሰቦች በዘፈቀደ ማሰራቸውን ቀጥለዋል።
ፍልሰተኞች ፣ ስደተኞች እና ጥገኝነት ጠያቂዎች
የኢትዮጵያ የጸጥታ ሃይሎች ኤርትራዊያን ስደተኞችን፣ ፍልሰተኞችን እና ጥገኝነት ጠያቂዎችን በኣዲስ ኣበባ እና ሌሎች የሀገሪቱ ክፍሎች በማሰባሰብ በዘፈቀደ ማሰራቸውን የሚገልጹ ዘገባዎች በግንቦት ወር መውጣት ጀመሩ። እ.ኤ.ኣ በመጋቢት 2020 የኢትዮጵያ ባለስልጣናት ኣዲስ ከኤርትራ የሚገቡ ጥገኝነት ጠያቂዎችን መመዝገብ ኣቆሙ።
ገለልተኛ የተባበሩት መንግስታት የባለሙያዎች ቡድን በሰኔ ወር መጨረሻ ላይ ኢትዮጵያ በመቶዎች የሚቆጠሩ ኤርትራውያንን ማፈናቀሏን ኣወገዘ። በተጨማሪ ባለስልጣናቱ ፍልሰተኞች፣ ጥገኝነት ጠያቂዎች እና ስደተኞች ላይ የሚያደሱትን የዘፈቀደ እስራት እና ማፈናቀል እንዲያቆሙ ኣሳስቧል።
በኣማራ ክልል ኣለምዋች ካምፕ የሚገኙ ኤርትራውያን ስደተኞችም በኣማራ ክልል የተቀሰቀሰውን ጦርነት ተከትሎ ማንነታቸው ባልታወቁ የታጠቁ ሃይሎች ጥቃት ደርሶባቸዋል።
የተባበሩት መንግስታት እና የዩናይትድ ስቴትስ ኣለም ኣቀፍ የልማት ኤጀንሲ (USAID) የተደገረው የምግብ ዕርዳታ ስራዎች እገዳ እ.ኤ.ኣ በ2023 ኣጋማሽ ላይ በኢትዮጵያ እየተስተናገዱ ለነበሩት ከ900,000 በላይ ስደተኞችን እና ጥገኝነት ጠያቂዎችን (በሱዳን ግጭት ከተቀሰቀሰ በኋላ የደረሱ ሱዳናውያንን ጨምሮ) ለብዙዎቹ የምግብ ኣቅርቦትን በእጅጉ ገድቧል።
ተጠያቂነት እና ፍትህ
በሰሜናዊ ኢትዮጵያ ግጭት ወቅት ለተፈፀሙት ጨምሮ ላለፉትም ሆነ ኣሁን እየደረሱ ላሉት ከባድ በደሎች ትርጉም ያለው ተጠያቂነት ኣልነበረም።
እ.ኤ.ኣ ህዳር 2022 የተደረገው የፀብ ማቆም ስምምነትን ተከትሎ የኢትዮጵያ መንግስት ተጠያቂነትን፣ ሓቅን፣ እርቅን እና ማገገምን ለማረጋገጥ ብሔራዊ የሽግግር የፍትህ ፖሊሲ ማዕቀፍ ተግባራዊ ለማድረግ ቆርጧል። እ.ኤ.ኣ. በጥር 2023 የኢትዮጵያ መንግስት ለህዝባዊ ምክክር መነሻ የሚሆን "የፖሊሲ ኣማራጮች ለሽግግር ፍትህ" (ኣረንጓዴ ወረቀት) በሚል ረቂቅ ኣውጥቷል። እንደ ኣማራ ክልል እና ኦሮሚያ ክልል ባሉ ኣሁንም በጦርነት የተጎዱ ኣካባቢዎችን ጨምሮ መንግስት በየካቲት ወር የህዝብ ኣስተያየት መሰብሰብ ጀምሯል። በመስከረም ወር በተባበሩት መንግስታት ድርጅት የሚተዳደረው የኣለም ኣቀፍ የሰብኣዊ መብት ኤክስፐርቶች ኮሚሽን (ICHREE) ሁለተኛ ሪፖርት እንደሚያሳየው መንግስት "የተፈጸሙ ጥሰቶችን በትክክል መመርመር ኣልቻለም" ብቻ ሳይሆን "የተሳሳተ የሽግግር የፍትህ ሂደት መጀመሩን" ኣረጋግጧል።
የፖለቲካ ተቃዋሚ ቡድኖች፣ የሲቪክ ማህበራት፣ የኢትዮጵያ የሰብኣዊ መብት ባለሙያዎች እና የምክክር ተሳታፊዎች ረቂቅ የፖሊሲ ሰነዱ በሉዓላዊነት መርህ ላይ ያተኮረ መሆኑ፣ ምክክሮቹ ሁሉንም በማካተት ረገድ እጥረቶች ያሉበት መሆኑ ተችተዋል። ውይይቱ ጦርነቶች እየተካሄዱ ባሉበት ወቅት መደረጉንም ጥያቄ ምልክት ዉስጥ አስቀምጠዉታል። በትግራይ ውስጥ ተሳታፊዎች ሰነዱ የኤርትራ ሃይሎች ተጠያቂነት ጉዳይ አለማየቱ ስጋታቸውን ኣንስተዋል ተብሏል።
በመጋቢት ወር በተባበሩት መንግስታት የሰብኣዊ መብቶች ምክር ቤት የICHREEን ስልጣን ያለጊዜው የሚያቋርጥ ውሳኔን ለማስተዋወቅ ሲዝት መንግስት በገለልተኛ የመብቶች ጥሰት ምርመራ ላይ ዘመቻውን ቀጥሏል። በተጨማሪም መንግስት የኣፍሪካ የሰብኣዊ እና ህዝቦች መብት ኮሚሽን የትግራይን ጉዳይ ኣጣሪ ኮሚሽን ጋር ለመተባበር ፈቃደኛ ሳይሆን ቀርቷል - ማጣራቱ ባገኛቸው ግኝቶች እና በምክረ ሃሳቦቹ ላይ ይፋዊ ሪፖርት ሳያወጣ በግንቦት ወር ኃላፊነቱን ኣብቅቷል።
ቁልፍ ዓለም ኣቀፍ ተዋናዮች
በጥር ወር የፈረንሳይ እና የጀርመን ውጭ ጉዳይ ሚኒስትሮች ወደ ኢትዮጵያ ተጉዘው የኣውሮፓ ህብረት ከመንግስት ጋር ያለውን ግንኙነት ወደ መደበኛው እንዲቀይር በቅድመ ሁኔታ ለሁለት ኣመታት በዘለቀው የትጥቅ ጦርነት ለተፈፀሙት መጠነ ሰፊ የመብት ጥሰቶች ተጠያቂነት እንዲኖር ግፊት ኣድርገዋል። በመጋቢት ወር የኣሜሪካ እና የኣውሮጳ ህብረት ኣባል ሀገራት የICHREEን ግዳጅ ያለጊዜው እንዲያበቃ የኢትዮጵያን ማስፈራሪያ በመከተል የICHREE መጪውን የመስከረም ሪፖርት “የመጨረሻ” በማለት ለመጥራት ተስማምተዋል። በጥቅምት ወር፣ ከዚህ ቀደም ኮሚሽኑን በታህሳስ 2021 የተቋቋመውን የውሳኔ ሃሳብ የመራው የኣውሮፓ ህብረት ሰብኣዊ መብቶች ምክር ቤት ስብሰባ የICHREEን ተልዕኮ የሚያድስ ወይም በኢትዮጵያ ያለውን የሰብኣዊ መብት ሁኔታ ኣለምኣቀፍ ቅኝት የሚያደርግ ምንም ኣይነት ረቂቅ የውሳኔ ሃሳብ ለሰብአዊ መብት ምክር ቤቱ ኣላቀረበም።
የኣውሮፓ ህብረት የውጭ ጉዳይ ምክር ቤት በሚያዝያ ወር የተጠያቂነት ኣስፈላጊነትን የሚያረጋግጥ ድምዳሜ ላይ ያሳለፈ ቢሆንም የኣውሮፓ ህብረት ወደፊት ከኢትዮጵያ ጋር ለሚኖረው ግንኙነት ቅድመ መስፈርቶቹ ዝቅ እንዲሉ ኣድርጓል። ይህም በግጭቱ መጀመሪያ ላይ እንዳደረገው ኢትዮጵያ ከ ICHREE ጋር እንድትተባበር ጥሪ ማቅረብ ኣለመቻሉን እና ፍትህን ጨምሮ ቁልፍ ጥያቄዎች ላይ መሻሻል ኣለመኖሩን ችላ ብሏል። በጥቅምት ወር የኣውሮፓ ህብረት የነበረው ግንኙነት ወደ ነበረው ለመመለስ ኣንድ እርምጃ ይሆናል ያለዉን ለኢትዮጵያ በ2020 መገባደጃ ላይ በትግራይ በተቀሰቀሰ ግጭት ምክንያት ተቋርጦ የነበረውን የ650 ሚሊዮን ዩሮ የእርዳታ ድጋፍ እንደሚሰጥ ኣስታውቋል።
በመጋቢት ወር የዩናይትድ ስቴትስ መንግስት በሰሜን ኢትዮጵያ በተቀሰቀሰው ግጭት የጦር ወንጀሎችን እና በሰው ልጆች ላይ የሚፈጸሙ ወንጀሎችን ጨምሮ ኣሰቃቂ ወንጀሎች መፈጸማቸውን ይፋዊ እውቅና ሰጥቷል። ከሶስት ወራት በኋላ፣ የጆ ባይደን ኣስተዳደር የኢትዮጵያ መንግስት “በከባድ የሰብኣዊ መብት ጥሰት ተግባራት” ላይ መሰማራት አለመቀጠሉን ኣንደሚያምን በሰኔ ወር ለኮንግረስ ኣሳውቋል። ይህን ተከትሎ ሀገሪቱ ዳግም ለኣሜሪካ እና ለኣለም ኣቀፍ ብድር እና ሌሎች የገንዘብ ድጋፎች ብቁ ሆናለች።
በመስከረም ወር አሜሪካ በ2021 በሰሜን ኢትዮጵያ ለሰብኣዊ መብት ረገጣ ተጠያቂ በሆኑ ግለሰቦች እና ኣካላት ላይ የማዕቀብ ስርዓትን ያቋቋመውን የስራ ኣስፈፃሚ ትዕዛዝ ኣድሳለች። እስካሁን ድረስ የኤርትራ ኣካላት እና ግለሰቦች ላይ ብቻ ነው ማዕቀብ የተጣለው።