Skip to main content

ኢትዮጵያ

Events of 2018

Abiy Ahmed, newly elected prime minister of Ethiopia, is sworn in at the House of Peoples' Representatives in Addis Ababa, April 2, 2018. 

© 2018 Hailu/Anadolu Agency/Getty Images

ለአመታት ሲካሄድ ከቆየ መጠነ ሰፊ የሆነ የመንግስትን ፖሊሲና የፀጥታ ሃይሉን አስከፊ ጭቆና ተቃውሞ በኋላ በሚያዚያ ወር ላይ አብይ አህመድ ጠቅላይ ሚኒስትር ሆነው መመረጣቸውን ተከትሎ በ2010 የሰብአዊ መብት አያያዝ ለውጥ ማሳየት ጀምሯል። መንግስት በሰኔ ወር የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁን በማንሳት በሺዎች የሚቆጠሩ የፖለቲካ እስረኞችን ከእስር ቤት ፈቷል። ከተፈቺዎች መሃል ጋዜጠኞችና ታዋቂ የፖለቲካ አመራሮች ያሉበት ሲሆን እስክንድር ነጋና መረራ ጉዲናም ከነዚህ ውስጥ ይገኙበታል። መንግስት በኢንተርኔት ላይ የጣለውን እቀባ በማንሳት፤የፀጥታ አስከባሪውም አሰራር በሃይል ላይ የተመሰረተ መሆኑን በማመን፤ አፋኝ ህጎችን የመቀየር ቁርጠኝነቱን በመግለፅና ብዙ አዳዲስ ለውጦችን በማስተዋወቅ ለተሻሻለ ሰብአዊ መብት አያያዝ ጥርጊያ መንገድ ከፍቷል።

በሃምሌ ወር ኢትዮጵያና ኤርትራ ለአስርት አመታት የቆየውን ግጭት በመፍታት የስላም ስምምነት ሲፈራረሙ በስምምነቱም ላይ የ1994ቱን የአለም አቀፉን የድንበር ኮሚሽን ውሳኔን በስራ ላይ ለማዋል ተስማምተዋል። በ1990 የሃገራቱ የጦር ሃይሎች  በባድመ ከተማ ላይ ጦርነት ካካሄዱ በኃላ የሃገራቱ ግንኙነት  በግጭት ላይ የተመሰረተ አለያም ተቀዛቅዞ  የከረመ ነበር ።

በሰኔ ወር ፓርላማው በሶስት ተቃዋሚ ቡድኖች  ማለትም ግንቦት ሰባት፥ የኦሮሞ ነፃ አውጪ ግንባር (ኦነግ) እና የኦጋዴን ብሔራዊ ነፃ አውጪ ግንባር (ኦብነግ) ላይ የተጣለውን ማእቀብ አንስቷል። መንግስት የተቃዋሚ አባሎችን፥ የመብት ተሟጋቾችንና ከቡድኖቹ ጋር ግንኙነት አላቸው ብሎ ያመነባቸውን ጋዜጠኞች እግዱን በማሳበብ አስከፊ ጥቃት ይፈጽምባቸው እንደነበር ይታወሳል። አሁን አብዛኛዎቹ የእነዚህና የሌላ ቡድን አባላቶች ከስደት ወደ ኢትዮጵያ እየተመለሱ ነው።

ገዢው ፓርቲ የኢትዮጵያ ህዝቦች አብዮታዊ ዴሞክራሲ ግንባር (ኢህአዴግ) የፓርላማውን መቀመጫ መቶ ፐርሰንት በተቆጣጠረበት ሁኔታ ተቋማቶቹና የህግ መሰናክሎቹ ዘላቂ ለሆነ የፖለቲካ ምህዳር ተግዳሮቶች መሆናቸው ይቀጥላል። ለአመታት የተፈፀሙ የሰብአዊ መብት ጥሰቶች፥ ማሰቃየቶች እና ከፍርድ ውጭ ግድያዎች ላይ ተጠያቂነትን ማምጣትና ለተቃዋሚዎችና ለሲቪክ ማህበራቶች ምህዳር መክፈት የአዲሱ አስተዳደር ዋና ተግዳሮቶች ናቸው።  ለውጡን መሸከም የሚችሉ ነፃ ተቋማት ባለመኖራችው የለውጡ ሂደት  ሊደናቀፍ የሚችልበት ምልክቶች አሉ።

በመስከረም ወር አዲስ አበባ ውስጥ በተካሄደ ሰላማዊ ሰልፍ ላይ የፀጥታ ሃይሎች አምስት ስዎችን ተኩሰው ገድለዋል። ሠልፈኞቹ  በወሩ መጀመሪያ ላይ ኦሮሚያ ውስጥ ለተፈፀመው በሃይል መፈናቀልና ብሄር ተኮር ጥቃት በተለይም አስገድዶ መድፈርና ግድያ መንግስትን ለዜጎች ተገቢውን ጥበቃ አላደረገም በሚል ተችተውታል። እየተካሄደ ያለው የብሄር ግጭትና መፈናቀል የሰዎችን ህይወት አደጋ ላይ እየጣለ ነው። የማህበረስባዊ እርስ በርስ ግጭቶችና ጥቃቶች አንዳንዴም የክልልና የአካባቢ ፀጥታ ሃይሎችን ባሳተፉ ግጭቶች የተነሳ ከሁለት ሚሊዮን በላይ ሰዎች በሃገር ውስጥ ተፈናቅለዋል።

በነፃ ሃሳብን መግለፅና መሰብሰብ

ኢትዮጵያ የፖለቲካዊ እንድምታ ባለው ክስ ታስረው ወይንም ተፈርዶባቸው የነበሩ እንደ እስክንድር ነጋና ውብሸት ታዬ አይነት ታዋቂ ፀሃፊዎችን ከስድስት አመት በላይ እስር በኋላ ፈታለች። የፌዴራል አቃቤ ህግ ቢሮ በጦማሪዎች ፥ ጋዜጠኞችና በውጭ ሃገር የሚገኙ ዳያስፖራ የመገናኛ ብዙሃን ድርጅቶች እንደ የኢትዮጵያ ሳተላይት ቴሌቪዥን (ኢሳት)፥ የኦሮሚያ ሚዲያ ኔትዎርክ (ኦኤምኤን) ከዚህ በፊት መንግስት በመተቸታቸው ብቻ አመፅ በማነሳሳት ብሎ ክስ የመሰረተባቸው ቢሆንም ማንኛውም አይነት በመጠባበቅ ላይ ያለ ክስ ውድቅ እንዲሆን አድርጓል።

ኦኤምኤን እና ኢሳት ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ በውጭ ሃገር ለሚንቀሳቀሱ የቴሌቪዥን ጣቢያዎች ያቀረቡትን ጥሪ ተከትሎ በሰኔ ወር  አዲስ አበባ ውስጥ ቢሮዎቻቸውን ከፍተዋል። በተጨማሪም መንግስት ከ250 በላይ ድህረ ገፆች ላይ የጣለውን እገዳ አንስቷል። በ2015ቱ ተቃውሞ ወቅት ተጥሎ የነበረው የኢንተርኔትና የሞባይል መተግበሪያዎች እገዳም ተነስቷል።

አብዛኛዎቹ ተቃውሞን ዝም ለማሰኘትና ትርጉም ያለውን የዜጎችን ተሳትፎ ለመገደብ የወጡ እንደ  የበጎ አድራጎት ማህበራት አዋጅ ፥ የመገናኛ ብዙሃን ህግ እና የፀረ ሽብር አዋጅ አይነት አፋኝ ህጎች ይህ ሪፓርት በሚጻፍበት ወቅት በማሻሻያ ሂደት ላይ ናቸው፡፡ 

ያለክስ ማቆየት፥ ማሰቃየትና በዘፈቀደ ማሰር

የኢትዮጵያ መንግስት ባለስልጣኖች የሚታመኑ ማስረጃዎች እያሉ እንኳን አብዛኛውን ጊዜ የማሰቃየት ክሶችን ይክዳሉ። ነገር ግን ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ በሃምሌው የፓርላማ ንግግራቸው ላይ መንግስት ማሰቃየትንና ህገወጥ የምርመራ ቴክኒኮችን በተጠርጣሪዎች ላይ ይጠቀም እንደነበረ አምነው ይህም በመንግስት የተፈፀም ሽብር ነው ብለዋል።

ኢትዮጵያ በአመቱ መጀመሪያ ላይ  የፖለቲካ እስረኞች ማሰቃያና ማንገላቻ መሆኑ የሚታወቀውን ማእከላዊ እስር ቤት ዘግታለች። መገናኛ ብዙሃኖች በእስር ቤቶች ያሉትን ጉልህ የሆኑ ቅሬታዎች ከዘገቡ በኋላ በሃምሌ ወር የጠቅላይ አቃቤ ህጉ ቢሮ አምስት የእስር ቤት ሃላፊዎችን ቢያሰናብትም ምንም አይነት ክስ ግን ሳይመሰርትባቸው ቀርቷል። አብዛኛዎቹ በክልል መስተዳደር ውስጥ የሚገኙ እስር ቤቶች አንዳንዶቹ በአጉል አያያዝ፤ በአስገድዶ መድፈር፤ማሰቃየት የሚታወቁና የመድሃኒትም ሆነ የህግ እርዳታ አቅርቦት ችግር ያለባችው ሲሆን በለውጡ ግን ምንም ያልተነኩ ናቸው።

በሃምሌ ወር ላይ የጠቅላይ አቃቤ ህግ ቢሮ በእስር ቤቶች ውስጥ የሚፈፀመው ማስቃየትና አላግባብ አያያዝ ላይ ምርመራ እንደሚካሄድ ለመገናኛ ብዙሃን ገልፆ ነበር። እንደ ጠቅላይ አቃቤ ህጉ በህዳር ወር  በርካታ የፀጥታ ሃይሉ ከፍተኛ ባለስልጣናት በተጠረጠሩበት የእስር ቤት ውስጥ መብት ጥሰት በቁጥጥር ስር ውለዋል። ይኸ መግለጫ እስከተፃፈበት ድረስ በተጠርጣሪዎቹ ላይ ምንም አይነት ክስ አልተመሰረተም።

መንግስት በ2007 እና በ2008 በኦሮሚያ እና በሌሎች ክልሎች በተካሄዱ መጠነ ስፊ ተቃውሞዎች ወቅት በተገደሉ ከ1000 በላይ ሰዎች ጉዳይ ላይ ምንም አይነት ምርመራ አላካሄደም። በጠቅላይ አቃቤ ህጉ ቢሮ ስር የሚገኘው የህግ እና ፍትህ ምክር ቤት  የፍርድ ስርአት ገለልተኝነት ማሻሻል ቁልፍ መሆኑን ቢገልፅም ሂውማን ራይትስ ዎች  በፌዴራልም ሆነ በክልል የተወሰደ ወሳኝ እርምጃ እንዳለ አያውቅም። ፍርድ ቤቶች አሁንም የስራ አስፈፃሚውን የፖለቲካ ውሳኔ በማስፈፀም ላይ ይገኛሉ።

የሶማሌ ክልል የመብት ጥሰቶች

የሶማሌ ክልል አምባገነን አመራርን  በማውገዝ የሚታወቁት ሙስጠፋ ኦማር፤አብዲ ሞሃመድ ኦማርን (አብዲ ኤሊ) በመተካት የክልሉ ፕሬዝዳንት ሆነው በነሃሴ ወር ላይ ተመርጠዋል። በተለይ በ1999  አማፂው ኦብነግ እና በኢትዮጵያ የጦር ሃይል መሃል ግጭቶች በመካረራቸው የአብዲ ኢሌ አገዛዝ ብዙ የሰብአዊ መብት ጥሰቶች ሲፈፅም ከርሟል።

ከ1999 አጋማሽ እስከ 2000 መጀመሪያ ድረስ በሁሉም ወገኖች የጦር ወንጀሎች ተፈፅመዋል። የኢትዮጵያ መከላከያ ሰራዊት በሰው ልጆች ላይ የሚፈፀሙ ወንጀሎች፤ ግድያዎች፥ ማስቃየቶች፥ አስገድዶ መድፈር እና በሃይል ማፈናቀል ክስ ሃላፊነቱን ሊወስድ ይገባል።

የኢትዮጵያ መንግስት በ2000 የአማፂያንን ጥቃት ለመከላከል በሚል ተጠሪነቱ በወቅቱ የክልሉ ፀጥታ ሃይል አዛዥ ለነበሩትና በኋላ ክልሉን በፕሬዝዳትነት ለ8 አመታት የመሩት አብዲ ኤሊ የሆነ ልዩ ፖሊስ አቋቋመ። ልዩ ፖሊሱ በክልሉና በአጎራባች ኦሮሚያ ክልል ውስጥ የመብት ጥሰቶችንና አንዳንዴም ግድያዎች ሲፈፅም ከርሟል።

በነሃሴ ወር ልዩ ሃይሉና ለአብዲ ኤሊ ታማኝ የሆኑ ወጣቶች ጅጅጋ ውስጥ ነዋሪዎች ላይ ጥቃት ከፈፀሙና ንብረት ካወደሙ ሁለት ሳምንት በኋላ ያንን ተከትሎ አብዲ ኤሊ ስልጣናቸውን ለቀው በቁጥጥር ስር ውለዋል። እስከ አሁንም ክስ ሳይመሰረትባቸው በመንግስት ቁጥጥር ስር ይገኛሉ። የፖሊስ አዛዥ የነበሩት አብዲላሂ ቡራሌ (በተለምዶ አብድራህማን ላብጎሌ በሚል ይታወቃሉ) በነሃሴ ወር ስልጣናቸውን የለቀቁ ሲሆን ግለሰቡ በሰብአዊ መብት ጥሰት ላይ እንደተሳተፉ ማስረጃዎች ቢኖሩም እንዲሁም እርሳቸውና ሌሎች የኢትዮጵያ መከላከያ ሰራዊት ሆኑ የልዩ ፖሊስ አባላት በሲቪሎች ላይ የመብት ጥሰት መፈፀማቸው ቢታወቅም እስካሁን ምንም አይነት ክስ አልተመሰረተባቸው።

በልዩ ፖሊስ በሚተዳደረው ኦጋዴን እስር ቤት ውስጥ እስረኞች ማሰቃየት ሲፈፀምባቸው፥ በቂ ህክምና ሳያገኙ፥ የቤተስብ ጉብኝትና ጠበቃ ሳይፈቀድላቸውና አንዳንዴም ምግብ ሳይቀርብላቸው ቆይተዋል። ሂውማን ራይትስ ዎች መግለጫ ካወጣ በኋላ በርካታ እስረኞች የተፈቱ ሲሆን ነሃሴ ወር ላይ የኦጋዴን እስር ቤት እንዲዘጋ ተደርጓል።

የሃገር ውስጥ መፈናቀል

ኢትዮጵያ በሃገር ውስጥ የተፈናቀለ 2 ሚሊዬን ህዝብ ሲኖራት 1 ሚሊዬን የሚያህለው ከሚያዚያ እስከ ሰኔ ባሉት ወራቶች በኦሮሚያና በደቡብ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ክልል ውስጥ በጌድዬና በጉጂ ማህበረሰቦች መሃከል በተነሳ ግጭት የተፈናቀሉ ናቸው::  በኦሮሚያና በሶማሌ ክልል ድጋሚ ባገረሸ ግጭት 145,000 ስዎች ተፈናቅለዋል:: በመስከረም ወር በአዲስ አበባ ዙሪያ በተፈፀመ ብሔር ተኮር ጥቃት 15,000 ሰዎች ተፈናቅለዋል:: ግጭቶች እንደሚከሰቱ ምልክቶች የታዩ ቢሆንም መንግስት ዜጎችን ከጥቃት ለመከላከል ሳይቻለው በመቅረቱ ተጨማሪ ሰዎች ለመፈናቀል ተዳርገዋል:: ሂውማን ራይትስ ዎች ቢሮ የፌዴራል መንግስቱ ለተፈናቃዬቹ ከሚያደርጋቸው ሰብአዊ እርዳታ ውጭ የውስጥ መፈናቀሉ እና የብሔር ግጭቶችን ለመከላከል መንግስት የሚያደርገውን ጥረት እንዳለ መረጃ የለውም::

ቁልፍ አለም አቀፍ ተዋናዬች

ኢትዮጵያ እያካሄደችው ላለው ለውጥ አለም አቀፍ ሙገሳዎች እየጎረፋላት ይገኛል። የአፍሪካ ህብረት መቀመጫ መሆኗ፤ ለአለም አቀፋ  የሰላም አስከባሪ ሃይል በምታደርገው አስተዋጽኦ፥ በቀጠናው ላይ ለምታበረክተው ፀረ ሽብር እንቅስቃሴና ለስደተኞች ባላት አጋርነት የተነሳ ከውጭ ለጋሽ ሃገሮችና ከቀጠናው አጎራባች ሃገሮች ጠንካራ ድጋፍ በማግኘት ላይ ነች::

የቀድሞው የተባበሩት መንግስታት የሰብአዊ መብት ኮሚሽነር የነበሩት ዛይድ ራድ አልሁሴን ኢትዮጵያን በጎበኙበት ወቅት በቅርብ ከእስር ከተፈቱ የፖለቲካ አመራሮችና የመንግስት ባለስልጣናት ጋር ውይይት አካሂደዋል። በውይይቱም ከመንግስቱ  የሰብአዊ መብት ኮሚሽን ገለልተኛና ተአማኒ ተቋም ማድረግ አስፈላጊነትን በአፅንኦት ተናግረዋል።

በሚያዝያ ወር የአሜሪካ የተወካዮች ምክር ቤት የኢትዮጵያ መንግስት የሰብአዊ መብቶች አያያዝ እንዲሻሻል፥ ለህግ የበላይነት እና ዴሞክራሲ እንዲሰራ የሚያበረታታ ውሳኔ አሳልፏል። አሜሪካ ለኢትዮጵያ የምታደርገውን ድጋፍ እንደምትቀጥልና በመካሄድ ላይ ያለውንም ለውጥ እንደምትደግፍ አስታውቃለች።

ኢትዮጵያ ምንም እንኳ የተባበሩት መንግስታት የፀጥታው ኮሚሽን እና የተባበሩት መንግስታት የሰብአዊ መብት ካውንስል አባል ብትሆንም ለተባበሩት መንግስታት መዋቅሮች ባለመተባበር ታሪኳ ትታወቃለች። ከ1998 ጀምሮ ለኤርትራ ከገባው የተባበሩት ልዩ ራፕርተር ውጭ ማንኛውም አይነት ልዩ ራፖርተር ወደ ሃገር እንዲገባ አልተፈቀደለትም።  በማሰቃየቶች ላይ፥ ሃሳብን በነፃነት የመግለፅና የመናገር መብት በስላማዊ መንገድ የመሰብሰብ መብት እና ሌሎች በርካታ ጉዳዮች የሚሰሩ ራፓርተሮች  ሃገር ውስጥ ገብተው ለመስራት እንዲፈቀድላቸው ጥያቄ አቅርበው ለአመታት እየጠበቁ ይገኛሉ።

ኢትዮጵያ በበርካታ ሃገሮች የሰብአዊ መብት አያያዝ ጉዳይ ላይ ከፀጥታ ካውንስሉ ጋር ሳትስማማ ቀርታለች። በሃምሌ ወር በድቡብ ሱዳን ላይ ለረጅም ጊዜ ሲጠበቅ የቆየውን የመሳሪያ ማዕቀብ ከመደገፍ ተቆጥባለች። ኢትዮጵያ በሶሪያ ላይ  የኬሚካል መሳሪያ ምርመራ እንዲካሄድ ድምፅ የሰጠች ቢሆንም የመጋቢቱን የፀጥታ ምክር ቤት የሰብአዊ መብት ከፍተኛ ኮሚሽነር በሶሪያ ሁኔታ ላይ የስጡትን መግለጫን ግን ሳትደግፍ ቀርታለች።