Skip to main content

ኢትዮጵያ

Events of 2019

በጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ የመጀመሪያ የስልጣን አመት የተተገበሩት የሰብዐዊ መብት አያያዝ ማሻሻያዎች በ2012 ዓ.ም በተፈጠሩት ማህበረሰባዊ እና የብሄር ግጭቶች እንዲሁም በሥርዓትና ህግ አለመከበር ምክንያት ስጋት ውስጥ ወድቀዋል።

 

መንግስት የመፈንቅለ መንግስት ሙከራ ብሎ ባለው የአማራ ክልል  የጥቅምት 15ቱ በከፍተኛ ባለስልጣናት ላይ የተፈፀመው ግድያ፤ እንዲሁም በአዲሰ አበባና ኦሮሚያ ክልል የታዋቂውን የፖለቲካ መብት ተሟጋችና የሚዲያ ባለቤት ጃዋር ሞሃመድ ጋር ተያይዞ በተከሰተው የማህበረሰብ ግጭት እና ፖለቲካዊ አለመረጋጋት  ለመጪው የ2012 ሃገር አቀፍ ምርጫ ወቅት ሊኖር የሚችለውን ውጥረት ተጨማሪ ማሳያ ሆኗል።

 

ፓርላማው ሃምሌ ወር ላይ ሲራዘም የከረመውን የህዝብ ቆጠራ ለሃገራዊ ምርጫ ልምምድ ያለውን ፋይዳ ችላ በማለት ለሌላ ጊዜ እንዲተላላፍ በድምፅ ብልጫ ወስኗል።

 

የተቋማት ማሻሻያዎች በተለይም የፍትህ ተቋማት ነፃነት እና የተጋጋለውን የብሔር ግጭት ሊያረግቡ የሚችሉ እንደ እውነትን ማረጋገጠ ፣ እርቅ እና ተጠያቂነትን ለማስፈን የተወሰዱ እርምጃዎች ውስን ነበሩ።

 

የመናገርና የመሰብሰብ ነፃነቶች

 

የሲዳማ ህዝብ በሃምሌ 11 2010 ዓ.ም ለፌዴራል መንግስት ከደቡብ ብሄር ብሄረሰቦችና ህዝቦች  ክልል (ደ/ብ/ብ/ሕ/ክ) ተነጥሎ ራስን በራስ ለማስተዳደር የሚያስችለውን የህዝበ ውሳኔ እንዲያካሂድ ጥያቄ አቅርቦ ነበረ ። የሲዳማ ህዝብ በደ/ብ/ብ/ሕ/ክ ውስጥ ካሉት ብሄሮች  ትልቁን የህዝብ ቁጥር የያዘ ሲሆን ክልል ለመሆን ጥያቄ በማቅረብም የመጀመሪያው የክልሉ ህዝብ ነው።

 

የፌዴራል መንግስት በህገ መንግስቱ ውስጥ የተገነዘበውን የህዝበ ውሳኔ ጥያቄ የአንድ አመት ገደብ ተከትሎ ማስፈፀም አልቻለም። ሃምሌ 11 በደ/ብ/ብ/ሕ/ክ ዋና ከተማ ሃዋሳ ህዝበ ውሳኔው እንዲካሄድ ለመጠየቅ ሰልፍ በወጡና በፀጥታ ሃይሎች መሃከል በተፈጠረ ግጭት እና እሱን ተከትሎ የሲዳማ ተወላጅ ባልሆኑ የክልሉ ነዋሪዎች ላይ በተፈፀመ ጥቃት 53 ሰዎች መገደላቸውን፤ በመቶዎች መፈናቀላቸውንና  በንብረት ላይ ከባድ ውድመት የደረሰ መሆኑን የዞኑ ፖሊስ ባለስልጣኖች አሳውቀዋል። ይህን ተከትሎም የደ/ብ/ብ/ሕ/ክ በፌዴራል የፀጥታ ሃይል ቁጥጥር ስር እንዲሆን ተደርጓል። ነሃሴ ወር ላይ የብሄራዊ ምርጫ ቦርድ በህዳር 3 ህዝበ ውሳኔውን አካሂዳለሁ ቢልም በኋላ ላይ ግን ወደ ህዳር 10 አዛውሮታል።

 

የጃዋር ሞሃመድን መንግስት ጠባቂዎቼን ሊያነሳብኝ ነው ክስ ተከትሎ ጥቅምት 12 በአዲስ አበባ  የተቀሰቀሰው ረብሻ ወደ ብዙ የኦሮሚያ ክፍሎች ሲሰራጭ የመንግስት የፀጥታ ሃይል በተለይም አምቦ ከተማ ላይ ተመጣጣኝ ያልሆነ የሃይል እርምጃ መውሰዱ ተስተውሏል። በብዙ ከተማዎች ውስጥ ረብሻው በፍጥነት ወደ ማህበረሰብ ግጭት ተሸጋግሯል። መንግስት 86 ሰዎች መገደላቸውን አምኖ ከዚህ ውስጥ አስሩ ከፀጥታ ሃይል ጋር በተደረገ ግጭት መሞታቸውን ገልጷል።

 

በጥር ወር ላይ መንግስት የሲቪክ ማህበረሰቡን ማደራጃ አዋጅ አፅድቆ ከዚህ በፊት ወጥቶ የነበረውን የገለልተኛ የሰብዕዊ መበት ሪፖርቶችን በማፈን የሚታወቀውን  የ2001 ዓ.ም የበጎ አድራጎት ድርጅቶች እና ማህበራት አዋጅ እንዲሻር ተስማምቷል። አዲሱ ህግ የከዚህ በፊቱን 10 በመቶ የውጭ ድጋፍን ገደብ አንስቷል። ሆኖም ህጉ የውጭ ሎቢንግ ላይ ያለውን እግድ አለማንሳቱ አሁንም ህጉ ላይ ስጋት እንዲኖር አድርጓል።

 

መንግስት በ2001 የፀደቀውንና የሀገሪቱን አፈኝ የነበረውን የፀረ ሽብር አዋጅ እንደገና አርቅቋል። ይህ ፁሕፍ በሚዘጋጅበት ወቅት ረቂቁ ለፓርላማ ቀርቦ ግምገማ እየተደረገበት ይገኛል። ሆኖም ግን በሰኔ ወር በአማራ ክልል ተፈፅሟል በተባለው መፈንቅለ መንግስት ሴራ የተነሳ ከደርዘን በላይ የሚሆኑ የአማራ ተወላጆች፣ ጋዜጠኞችን ጨምሮ የፀረ ሽብር ህጉ የጊዜ ቀጠሮ አንቀፅ ተጠቅሶ በእስር ላይ ይገኛሉ።  ይህ ፁሕፍ በሚዘጋጅበት ወቅት 13 የሚሆኑ እስረኞች ግልፅ ባልሆነ ሂደት የፀረ ሽብር ህጉ  ከሚፈቅደው አራት ወራት የጊዜ ቀጠሮ በላይ ክስ ሳይመሰረትባቸው በጊዜያዊ ማቆያ ቦታዎች ላይ ታስረው ይገኛሉ። አስራ ሁለቱ የፖለቲካ ተቃዋሚ ድርጅት አባል ሲሆኑ ከነዚህም ሰባቱ  የዘውግ ብሄርተኛ የሆነው  የአማራ ብሔራዊ ንቅናቄ (አብን) አባል፣ ቀሪዎቹ አምስቱ ደግሞ የአማራ የባህል መብት አራማጆች ንቅናቄ አባል ናቸው።

 

ጥር 16 2011 መንግስት በአዲስ አበባ ዙሪያ የሚያካሂደውን በሃይል ማፈናቀል ነው የተባለውን የቤት ማፍረስ ሂደት እየዘገቡ የነበሩትን የግል መገናኛ ብዙሃን የሆነው የመረጃ ቲቪ ሁለት ጋዜጠኞች የኦሮሚያ ፖሊስ በጊዜያዊነት በቁጥጥር ስር ካዋለ በኃላ ፈቷቸዋል። ከተፈቱ በኃላ በአካባቢው በነበሩ ወጣቶች ጥቃት የተፈፀመባቸው ሲሆን አንደኛውን በዱላ ሲደበድቡት ፖሊስ በአካባቢው ሆኖ ይመለከት ነበር ተብሏል። ከጥቃቱ ጋር ተያይዞ ማንም ሰው በቁጥጥር ስር አልዋለም።

 

በሃምሌ 11 መንግስት ማስፈፀም ያቃታውን ህዝበ ውሳኔ አለመካሄድ ተከትሎ በተነሳው ረብሻ ምክንያት የመንግስት የፀጥታ ሃይሎች የሲዳማ ሚዲያ ኔትዎርክ አባል የሆኑ ሰራተኞችንና የቦርድ አባላትን በቁጥጥር ስር በማዋል በሃዋሳ የሚገኘውን ጣቢያ መዝጋቱን መገናኛ ብዙሃን ዘግበዋል። ሃምሌ 16 ሰራተኞቹ ወደ ስራ ገበታቸው እንዲመለሱ የተፈቀደላቸው ቢሆንም በቁጥጥር ስር የዋሉት ግን ለሳምንታት ካለምንም ክስ በእስር ላይ እንዲቆዩ ተደርጓል።

 

በሚያዚያ ወር መንግስት በማህበራዊ ሚዲያ  በተለይም በፌስ ቡክ ላይ እየተሰፋፋ የመጣውን የጥላቻ ንግግር መስመር ለማስያዝ የጥላቻ ንግግር አዋጅ አውጥቷል። የጥቅምት ወሩን የማህበረሰብ ግጭት  ተከትሎ የሚኒስትሮች ምክር ቤት ረቂቁን አፅድቋል። ቀደም ያሉት የህጉ ረቂቆች አሻሚ የሆኑ የጥላቻ ንግግር ትርጉም የያዘ ሲሆን፣ ትርጓሜው የአመፅ  ማነሳሳትን፣ ማግለልን እና ህገወጥነትን የሚመለከት ሆኖ በጠባቡ ካልተተረጎመ በስተቀር ተቀባይነት ያላቸው የሃሳብ ልዩነትን የሚያሳዩ ንግግሮች ለማፈን ሊውል ይችላል።

 

መንግስት ኢንተርኔት መዝጋቱን ቀጥሏል። የሰኔ 15ቱን የመፈንቅለ መንግስት ሙከራ ነበር የተባለውን ተከትሎ በአጠቃላይ ሃገሪቱ የኢንተርኔት አገልግሎት መቋረጡንና እስከ ሰኔ 25 ድረስ  ሙሉ በሙሉ አገልግሎት መስጠት አለመጀምሩን አስመልክቶ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ለሚዲያ ሲያብራሩ ኢንተርኔት አየር ወይንም ውሃ አይደለም ብለዋል። በሰኔ ወር መጀመሪያ ላይ መንግስት ካለ ምንም አይነት ማብራሪያ ለአንድ ሳምንት ያህል ኢንተርኔት ዘግቷል።

 

ህገወጥ እስር፣ የቀድሞ የመብት ጥሰቶችን በዝምታ ማለፍ

 

በመስከረም ወር ላይ በመሃል አዲስ አበባ የሚገኘው በማሰቃያነትና በመጨቆኛነት የሚታወቀው አስፈሪው ማእከላዊ ፖሊስ ጣቢያ ከተዘጋ ከአንድ አመት በኋላ ለመጀመሪያ ጊዜ ለህዝብ ክፍት ሆኗል።

 

ምንም እንኳን የህገወጥ እስር ዘገባዎች በስፋት ባይኖሩም በኦሮሚያ ከዚህ ቀደም ታግዶ በነበረው የኦሮሞ ነፃነት ግንባር (ኦነግ) እና የመከላከያ ሃይል መሃል ውጊያ በተካሄደባቸው አካባቢ ባሉ የኦነግ አባላትና በደጋፊነት የተጠረጠሩ ሰዎች  ላይ መብት በጣሰ መልኩ እስር እየተካሄደ ይገኛል።

 

በሃምሌ 2011 ከተካሄደው የከፍተኛ ባለስልጣኖች እስር በቀር ከዚህ ቀደም ለተፈፀሙ ወንጀሎች ተጠያቂነት ለማምጣት የተደረገ ብዙም ጥረት የለም። በታህሳስ 2011 የብሄራዊ እርቅ ኮሚሽን ቢመሰረትም ሃላፊነቱ ግን በግልፅ አልተቀመጠም። በኢትዮጵያ ሶማሌ ክልል በአስፈሪነቱ የሚታወቀውንና አካላዊ ስቃይ፣ አስገድዶ መድፈር፣ እና ግድያ ይፈፀምበት የነበረውን የኦጋዴን እስር ቤት ሲያስተዳድሩ በነበሩ ባለስልጣኖች ላይ በእነርሱ ትእዛዝ ለተፈፀሙ ወንጀሎች የተፈረደባቸው ቢሆንም የፍርድ ሂደቱ ግን ለህዝብ ግልፅ አልነበረም።

 

ከግጭት ጋር የተያያዘ የሀገር ውስጥ መፈናቀል

 

ለረጅም ጊዜ የቆዩ ቅሬታዎች፣ የመሬት ባለቤትነት ጥያቄ፣ ውስብስብ የሆኑ የማንነት ጥያቄዎች እና የውስጥ ድንበር ማካላል ጋር ተያይዞ በተነሱ የብሄር ግጭቶች ለግድያዎችና ከፍተኛ ለሆኑ መፈናቀሎች መንሰኤ ሆነዋል።

 

በግጭት ምክንያት የተፈናቀሉ ሰዎች ቁጥር አሁንም ከፍተኛ ነው።  እንደ አለም አቀፍ የስደተኞች ጉዳይ ዘገባ ከሆነ እስከ ሃምሌ ወር ባለው ወደ 1.6 ሚሊዮን የሚጠጉ ሰዎች የተፈናቀሉ ሲሆን ከዚህ ውስጥ 66.4 በመቶው በግጭት ምክንያት የተፈናቀሉ ናቸው። የአለም አቀፍ ተፈናቃዮች ክትትል ቢሮ እንዳለው ደግሞ በኦሮሚያ፣ አማራ፣ ሶማሊያና በደቡብ ክልል የተከሰቱ የብሄር ግጭቶች እስከ 2011 አጋማሽ ለተፈፀመው ወደ 522,000 ለሚሆኑ ሰዎች መፈናቀል መንስኤ ሆኗል።

 

ከመጋቢት እስከ ግንቦት ባለው ጊዜ ውስጥ መንግስት ወደ 1.5 ሚሊዮን የሚጠጉ ተፈናቃዮች  ወደ ቀያቸው የመለስ ቢሆንም አብዛኛዎቹ  የደህንነት ስጋት ያለባቸው ሲሆን በተጨማሪም የሰብዐዊ እርዳታ እገዳ ተደርጎባቸው የመጠለያ ጣቢያዎች እንዲፈርስ ተደርጓል። የተመለሱትም ባለው የፀጥታ ችግር ምክንያት ለድጋሚ መፈናቀል የተዳረጉ ሲሆን ተጨማሪ የሰብዐዊ ድጋፍ ባለመኖሩ ለችግር ተጋልጠዋል።

 

የአለም አቀፉ የቀይ መስቀል ኮሚቴ ከ11 ዓመት በኃላ ለመጀመሪያ ጊዜ ወደ ሶማሌ ክልል ተጋብዞ ከኢትዮጵያ ቀይ መስቀል ጋር በመተባበር በማህበረሰብ ጥቃት ሰለባ ለሆኑ ሰዎች የድንገተኛ ጊዜ እርዳታ ማከፋፈል ችለዋል።

 

ውስብስብ እና ፖለቲካዊ እንድምታ ያለው በአዲስ አበባ ዙሪያ ያለው የመስፋፋትና ግልፅነት የሚጎለው በህገ መንግስቱ ውስጥ የተካተተው የኦሮሚያ ልዩ ጥቅም ጉዳይ መልስ ያላገኘ በመሆኑ ለተጨማሪ ውጥረት ምንጭ ሆኗል። በየካቲት ወር ላይ የኦሮሚያ ክልላዊ መንግስት በአዲስ አበባ ዙሪያ በህገወጥ መንገድ ተገንብተዋል ያላቸውን 12,000 መኖሪያ ቤቶች ለማፍረስ ማቀዱ ውጥረቱን እንዲባባስ አድርጓታል።

 

ቁልፍ የሆኑ አለም አቀፍ ተዋናዮች

 

ኢትዮጲያ የአፍሪካ ህብረት መቀመጫ በመሆኗ፣ በተባበሩት መንግስታት ውስጥ ሰላም ማስከበር ላይ ባላት አስተዋፆ እና በቀጠናው ውስጥ በምታደርጋቸው የአደራዳሪነት ሚና፣ በፀረ ሽብር ላይ እና በስደተኞች ጉዳይ ላይ ከምእራባዊያን ጋር ባላት ሽርክና የተነሳ ከለጋሽ ሃገሮች እና ከአብዛኛው አጎራባች ሃገሮች የሚደረግላት ድጋፍ ተጠናክሮ ቀጥሏል።

 

በጥቅምት ወር ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ ላሳዩት የሰላምና አለም አቀፍ ትብብር እናም ከኤርትራ ጋር ለፈጠሩት የሰላም ስምምነት የአለም አቀፉን የኖቤል ሽልማት እንዲሸለሙ ቢደረግም በድርድሩ ዙሪያ ላይ ያሉ አወዛጋቢ ጉዳዮች እና በተጨማሪም በሁለቱ ሃገሮች መሃል ያለው የድንበር ማካለል መፍትሄ ያላገኘ ጉዳይ እንደሆነ ቀጥሏል።

 

የሱዳኑን ፕሬዝዳንት ኦማር አልበሽር ከስልጣን መፈናቀል ተከትሎ በሚያዚያ ወር ላይ በመከላከያውና በሲቪሊ ፓርቲዎች መካከል ጠቅላይ ሚኒስትሩ ውይይት እንዲኖርና የሽግግር መንግስት እንዲመሰረት ከአፍሪካ ህብረት ጋር በመሆን ጥረት አድርገዋል። ሆኖም ግን የአባይ ወንዝን አጠቃቀም አስመልክቶ ከግብፅ  ጋር ያለው ውጥረት ተጋግሏል።

 

በጥቅምት 2012 ላይ የአውሮፓ ህብረት  ለምርጫ ማካሄጃ እገዛ ከመደበው  € 10 ሚሊዮን ( $10 ሚሊዮን) ውስጥ € 7ሚልዮን ( $7̇.8 ሚሊዮኑን) ሰጥቷል። ሆኖም ይህ ፅህፍ እስኪዘጋጅ ድረስ የአለም አቀፍ ምርጫ ታዛቢን አስመልክቶ የተቀመጠ ምንም አይነት እቅድ የለም።

 

በ2012 አለም አቀፍ ውቅታዊ ግምገማ መሰረት ኢትዮጵያ ለቀረበላት ለልዩ ሂደት በተናጠል ለቀረበላት ጥያቄ በጎ ምላሽ የሰጠች ሲሆን ከ1998 በኋላ ለመጀመሪያ ጊዜ ስልጣን ያለው አካል እንዲጎበኝ ፈቅዳለች። የተባበሩት መንግስታት ልዩ ራፖርተር ሃሳብን በነፃነት የመግለፅን መብት አስመልክቶ በታህሳስ ወር ላይ ጉብኝት ያደርጋል።  ማሰቃየትን አስመልክቶ የቀረበው የልዩ ራፖሩ ጥያቄ ግን ምላሽ በመጠባበቅ ላይ ይገኛል።

 

ከ 100000 በላይ የሆኑ ኢትዮጵያውያኖች ከሳውዲ አረቢያ የተባረሩ ሲሆን አብዛኛዎቹ ምንም አይነት ንብረት፣ ለምግብ የሚሆን ገንዘብ፣ ትራንስፖርት እና መጠለያ የሌላቸው ናቸው። የኢትዮጵያ መንግስትም ሆነ አለም አቀፉ ማህበረሰብ ለተባራሪዎቹ የሚሆን የመንና ሳውዲ አረቢያ ላይ ለደረሰባቸው አካላዊም ሆነ መንፈሳዊ ጥቃት ማገዣ የህክምና እርዳታ፣ መጠለያ ወይንም ወደ አካባቢያቸው ተመልሰው ከህብረተስቡ ጋር ተቀላቅለው ሊኖሩበት የሚችሉብት በቂ በጀት አልመደቡላቸውም።