Skip to main content

የ 2015 የዓለም የሰብአዊ መብቶች ሁኔታ ሪፖርት፡- ኢትዮጵያ

Dassanech (“What will happen when hunger comes?”)

© 2007 Brent Stirton/Reportage for Getty Images

Keynote

 
Tyranny’s False Comfort

Why Rights Aren’t Wrong in Tough Times

Essays

 
Internet en la encrucijada

Cómo la vigilancia del gobierno amenaza nuestra forma de comunicarnos

 
Deadly Cargo

Explosive Weapons in Populated Areas

 
Placer la barre plus haut

Événements sportifs de grande envergure et droits humains

የኢትዮጵያ መንግስት በተቃዋሚዎች ላይ የሚያደርገውን ጫና ከግንቦት 2015 ዓ.ም. ምርጫ አስቀድሞ ረገብ ሊያደርግ ይችላል የሚለው ተስፋ በ2014 ዓ.ም. መና ሆኗል።

ይልቁንም የጋዜጠኞች፣ የጦማሪያን፣ የተቃውሞ ሰልፈኞች እና የተቃዋሚ ፓርቲ ደጋፊዎችን ልሳን ለመዝጋት መንግስት የሚያደርገውን የዘፈቀደ እስር  እና ውንጀላ ቀጥሎበታል፤ ፖሊስ የተቃውሞ ሰልፈኞች ላይ ከተገቢው በላይ ሃይል ይጠቀማል፤ እንዲሁም ዓለማቀፍ መለኪያዎችን ይጥሳሉ በሚል በተባበሩት መንግስታት የሰብዓዊ መብቶች ምክር ቤት የኢትዮጵያ ዩኒቨርሳል ፒርዮዲክ ሪቪው/ግምገማን ጨምሮ በተለያዩ ዓለማቀፍ መድረኮች ውግዘት እየቀረባበቸው የሚገኙ አፋኝ ሕጎችን ለማሻሻል መንግስት ምንም የፈቃደኝነት ምልክት አላሳየም።

በሰላም የመሰብሰብ ነጻነት
የፀጥታ ሃይሎች የኢትዮጵያ ተቃዋሚ ፓርቲ መሪዎችና ደጋፊዎች ላይ ጥቃት ፈጽመዋል እንዲሁም አስረዋል፡፡ በሐምሌ ወር የሰማያዊ ፓርቲ፣ የአንድነት ለዴሞክራሲ እና ለፍትህ ፓርቲ እና የአረና ትግራይ ፓርቲ መሪዎች ታስረው በቁጥጥር ስር ውለዋል፡፡ ይህ ሪፖርት እየተዘጋጀ እስከነበረበት ጊዜ ድረስ ክስ ሳይመሰረትባቸው በእስር ላይ ይገኛሉ፡፡

በ2014 ዓ.ም. ሰማያዊ ፓርቲ የተቃውሞ ሰልፍ ለማካሄድ ያደረጋቸው ሙከራዎች በተደጋጋሚ ታግደውበታል፡፡ ፓርቲው ሰላማዊ ሰልፍ ለማካሂድ ያቀረባቸው ማመልከቻዎች ቢያንስ ሶስት ጊዜ ተቀባይነት ያላገኙ ሲሆን  የሰልፎቹ አስተባባሪዎችም እንደዚሁ ታስረዋል፡፡ በዓመቱ ውስጥ የመንግስት አካላት የተቃዋሚ ፓርቲ መሪዎችን በተደጋጋሚ አዋክበዋል፣ አስፈራርተዋል እንዲሁም አስረዋል፡፡

በሰኔ ወር የብሪታኒያ ዜጋ የሆነው እና በስልጣን ላይ ያለውን መንግስት በትጥቅ ትግል ለማስወገድ የሚንቀሳቀስ በመሆኑ ምክንያት የታገደው የግንቦት ሰባት ድርጅት ዋና ጸሃፊ አንዳርጋቸው ጽጌ ወደ ሌላ ሃገር ለመሻገር የመን በደረሰበት ጊዜ ተይዞ ለኢትዮጵያ ተላልፎ ተሰጥቷል፡፡ ወደ ኢትዮጵያ ተላልፎ የተሰጠበት መንገድ አንድ ሰው ማሰቃየት ወይም ሌላ ያልተገባ አያያዝ ሊገጥመው ወደሚችልበት ሃገር ተላልፎ እንዳይሰጥ የሚከለክለውን ዓለምዓቀፍ ህግ የጣሰ ነው፡፡ አንዳርጋቸው ግንቦት ሰባት ድርጅት ውስጥ ባለው ተሳትፎ ምክንያት በኢትዮጵያ በሌለበት ሁለት ጊዜ የሞት ፍርድ ተፈርዶበታል፡፡ ኢትዮጵያ ውስጥ ከስድስት ሳምንታት በላይ ማንም እንዳያገኘው ተደርጎ የታሰረ ሲሆን የቤተሰብ አባል፣ የህግ አማካሪ ወይም የዩናይትድ ኪንግደም የቆንስላ ተጠሪዎች እንዲያገኙት አልተፈቀደም፡፡ አሁንም ባልታወቀ ስፍራ እንደታሰረ ይገኛል፡፡

መንግስት በሃይማኖታዊ ጉዳዮቻቸው ላይ የሚያደርገውን ጣልቃ ገብነት የሚቃወሙ የተወሰኑ የሙስሊም ማህበረሰብ ክፍሎች የሚያካሂዱትን የተቃውሞ እንቅስቃሴ በ2014 ዓ.ም. የቀጥሉበት ቢሆንም የተቃውሞ እንቅስቃሴዎቹ እንደቀደሙት ዓመታት በተደጋጋሚ አልተካሄዱም፡፡ ይሁንና የጸጥታ ሃይሎች በ2013 ዓ.ም. እንዳደረጉት ሁሉ በእነዚህ የተቃውሞ ሰልፎች ላይም ከተገቢው በላይ ሃይል ተጠቅመዋል እንዲሁም የዘፈቀደ እስር ፈጽመዋል፡፡ በሐምሌ ወር 2012 ዓ.ም. የታሰሩት እና የፀረ-ሽብር አዋጁን በመጣስ ክስ የቀረበባቸው ሃያ ዘጠኙ የተቃውሞው መሪዎች ላይ የተጀመረው የፍርድ ቤት ሂደትም እንደቀጠለ ነው፡፡

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ድንበርን በከተማዋ ዙሪያ ወደሚገኙት አዋሳኝ የኦሮሚያ ክልል አካባቢዎች ለማስፋፋት የተዘጋጀውን ዕቅድ በመቃወም በሚያዚያ እና ግንቦት ወራት በመላው የኦሮሚያ ክልል በሚገኙ ከተሞች ተቃውሞዎች ተነስተዋል፡፡ የጸጥታ ሃይሎች በበርካታ ከተሞች የሚገኙ የተቃውሞ ሰልፈኞች ላይ ጥይት መተኮስን ጨምሮ ከተገቢው በላይ ሃይል ተጠቅመዋል፡፡ ቁጥራቸው ከሃያ በላይ የሚሆን ሰዎች መገደላቸው የተረጋገጠ ሲሆን በመቶዎች የሚቆጠሩ ታስረዋል፡፡ በርካቶቹ ክስ ሳመሰረትባቸው በእስር ላይ ይገኛሉ፡፡

የሰብዓዊ መብቶች ጉዳይን በሚከታተሉ ድርጅቶች እና በነፃ መገናኛ ብዙሃን ላይ የተጣሉት ገደቦች የደረሱ ጉዳቶችን እና የተፈጸሙ እስሮችን መጠን በትክክል ለማወቅ እንዳይቻል አስቸጋሪ ሁኔታ ፈጥረዋል፡፡ ተቃውሞ የሚደረግባቸው ቦታዎች ላይ ለመድረስ ሙከራ ያደረጉ የውጭ ጋዜጠኞች በጸጥታ ሰዎች እንዲመለሱ ተደርጓል አሊያም ተይዘዋል፡፡ ኦሮሞዎች ከጠቅላላው የኢትዮጵያ ሕዝብ ወደ 45 በመቶ የሚሆነውን ብዛት የሚይዙ ሲሆን ከታገደው የኦሮሞ ነጻነት ግንባር (ኦነግ) ጋር ግንኙነት አላችሁ በሚል የዘፈቀደ እስር ይፈጸምበቸዋል፤ ውንጀላም ይደርስባቸዋል።

የመደራጀት ነጻነት
በ2009 ዓ.ም የወጣው የበጎ አድራጎት ድርጅቶች እና ማህበራት አዋጅ መንግስታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች በሰብዓዊ መብቶች ዙሪያ የመስራት አቅማቸውን በእጅጉ ይገድባል፡፡ ህጉ በሰብዓዊ መብቶች፣ በመልካም አስተዳደር፣ በግጭት አፈታት፣ እና በሴቶች፣ ህፃናት እና የአካል ጉዳተኛ ሰዎች መብቶች ላይ የአድቮኬሲ ስራ የሚያከናውኑ ድርጅቶች ከገቢያቸው ከ10 በመቶ በላይ ከውጭ ምንጮች መቀበል እንደማይፈቀድላቸው ይደነግጋል። በ2014 ዓ.ም. ሕጉ ተጠናክሮ ሥራ ላይ ውሏል።

በመጋቢት ወር ኢትዮጵያ በነዳጅ ዘይት እና ማእድን ዘርፎች የሚገኝ ገቢን በተመለከተ ግልጽነት እንዲሰፍን የሚያበረታታው የኤክስትራክቲቭ ኢንደስትሪስ ትራንስፓረንሲ ኢኒሼቲቭ (Extractive Industries Transparency Initiative (EITI)) አባል ሆናለች፤ ይሁንና አባል ለመሆን የሚያመለክቱ ሃገራት ማሟላት ከሚጠበቅባቸው  መስፈርቶች አንዱ የተፈጥሮ ሃብት አስተዳደርን በተመለከተ በሚደረጉ ውይይቶች ላይ ነጻ ወገኖች ትርጉም ያለው ተሳትፎ ማድረግ እንዲችሉ ለማስቻል ያላቸውን ቁርጠኝነት ማሳየት ነው፡፡ የበጎ አድራጎት ድርጅቶች እና ማሕበራት አዋጁ አሳሳቢ ሁኔታ በመፍጠሩ ምክንያት ኢትዮጵያ  የዚህ ኢኒሼቲቭ አባል ለመሆን አቅርባ የነበረው ማመልከቻ በ 2010 ዓ.ም. ውድቅ ተደርጎ ነበር፡፡

ሃሳብን የመግለጽ ነጻነት
መገናኛ ብዙሃን በመንግስት ከፍተኛ ቁጥጥር ውስጥ እንዳሉ የቀጠሉ ሲሆን ይህም ጋዜጠኞች የራስ ቅድመ-ምርመራ ማድረግ አልያም ለጥቃት ፣ ለእስር ወይም ለስደት መዳረግን እንዲመርጡ አስገድዷቸዋል፡፡ በ2014 ዓ.ም. በሃያዎች የሚቆጠሩ ጋዜጠኞች እና ጦማሪያን የደረሰባቸውን ማስፈራሪያ ተከትሎ ሃገር ለቀው ተሰደዋል፡፡ በነሃሴ ወር 2014 ዓ.ም. ስድሰት የግል ጋዜጣ ባለቤቶች ህትመቶቻቸውን በተመለከተ ረዥም ጊዜ የቆየ የማስፈራሪያ እና የማጥላላት ዘመቻ ከተካሄደባቸው በኋላ ክስ ተመስርቶባቸዋል፡፡ እንደ ኮሚቴ ቱ ፕሮቴክት ጆርናሊስትስ (Committee to Protect Journalists) መረጃ አትዮጵያ በዓለም ላይ ከፍተኛ ቁጥር ያላቸው ጋዜጠኞች ከተሰደዱባቸው ሶስት ሃገሮች አንዷናት፡፡

ከ2009 ዓ.ም ጀምሮ የፀረ-ሽብር አዋጁ የፖለቲካ ተቃዋሚዎችን ለማጥቃት፣ ተቀናቃኞችን ለማፈን፣ እና ጋዜጠኞችን ፀጥ ለማሰኘት ጥቅም ላይ ውሏል፡፡ የኢትዮጵያ መንግስት ዞን ዘጠኝ በመባል የሚታወቁ 10 ጦማሪያንን እና ጋዜጠኞችን ከ80 ቀናት በላይ ክስ ሳይመሰረትባቸው በእስር እንዲቆዩ ካደረገ በኋላ በሐምሌ ወር  በጸረ-ሽብር አዋጁ መሰረት ክስ እንዲመሰረትባቸው አድርጓል፡፡ ክሱ እግድ ከተጣለባቸው ተቃዋሚ ድርጅቶች ጋር ግንኙነት ማድረግ እና በአመጽ መንግስትን ለማስወገድ መሞከር የሚል ተካቶበታል፡፡ ጦማሪያኑ የኢትዮጵያን ወቅታዊ ሁኔታ የሚዳስሱ ጉዳዮች ላይ በየጊዜው ይጽፉ ነበር፡፡ ከቀረቡባቸው ማስረጃዎች መካከል ሴኩሪቲ ኢን ኤ ቦክስ የተባለ ማንም ሰው ሊያገኘው የሚችልና የሰብዓዊ መብት ተሟጋቾች የሚጠቀሙት የስልጠና መሳሪያን/ማንዋል መጠቀምና ኬንያ ውስጥ በተሰጠ የዲጂታል ደህንነት  ስልጠና  ላይ ተሳትፋችሗል የሚል ነው፡፡ የፍርድ ሂደቱ ሕጋዊነት ላይ ጥያቄ የሚያስነሱ በርካታ ግድፈቶች ተፈጽመዋል።

በፀረ-ሽብር አዋጁ መሰረት ተከሰው የተፈረደባቸው እስክንድር ነጋ፣ ርዕዮት አለሙ እና ውብሸት ታየን ጨምሮ ሌሎች ጋዜጠኞችም እስካሁን በእስር ላይ ይገኛሉ፡፡

መንግስት እምብዛም ጠንካራ ትችት የማያቀርቡ ድረ-ገጾችን እና ብሎጎችን ሳይቀር ማገዱን ቀጥሎበታል፡፡ አብዛኛዎቹ የተቃዋሚ መገናኛ ብዙሃን ድረ-ገጾች እንዳይታዩ ታግደዋል፤ እንዲሁም የመገናኛ ብዙሃን ውጤቶች በሃገሪቱ ውስጥ ስራቸውን እንደቀጠሉ ለመቆየት ሲሉ በመንግስት ላይ የሚያቀርቡት ትችት ውሱን እንዲሆን ለማድረግ ተገደዋል፡፡

መንግስት በቤተሰብ አባላት መካከል እንዲሁም በጓደኞች መካከል የሚደረጉ   የስልክ ልውውጦችን በተለይም  ከውጭ ሃገር የሚደረጉ  ጥሪዎችን በመደበኛነት ይከታተላል፣ ይቀርጻል፤  እነዚህን የተቀረጹ የስልክ ልውውጦች እግድ ከተጣለባቸው ድርጅቶች ጋር ግንኙነት አላችሁ በሚል የተወነጀሉ ታሳሪዎች ምርመራ በሚደረግባቸው ወቅት እንዲያዳምጧቸው ይደረጋል፡፡የተቃውሞ ሰልፍ በሚደረግባቸው ወቅቶች የተንቀሳቃሽ ስልኮች ኔትወርኮች ይዘጋሉ እንዲሁም ከተንቀሳቃሽ ስልኮቻቸው በሚገኝ መረጃ በተቃውሞ ሰልፎች የተሳተፉ ሰዎች የሚገኙበት ቦታ ይለያል፡፡ አንድ ግለሰብ በግል ኮምፒውተሩ ላይ የሚተይባቸውን እያንዳንዷን ፊደል መመዝገብ እና የስካይፕ ልውውጦችን ጨምሮ ኮምፒውተሮችን በመጠቀም የሚያከናውነውን ማንኛውንም ተግባር የሚከታተሉ በጣም የረቀቁ የመሰለያ ሶፍትዌሮችን በመጠቀም መንግስት የዲጂታል ግንኙነቶችን ይከታተላል፡፡ ብቸኛ በሆነው የመንግስት ቴሌኮም አገልግሎት ሰጪ ተቋም ኢትዮ-ቴሌኮም አማካኝነት መንግስት በተንቀሳቃሽ ስልኮች እና ኢንተርኔት አገልግሎት ላይ ያለው ያልተገደበ ባለቤትነት ይህንን ክትትል የማድረግ አቅሙን የበለጠ አመቻችቶለታል፡፡

በስደት ላይ የሚገኙ ሰራተኞች ላይ የሚደርስ ጥቃት
በመቶ ሺዎች የሚቆጠሩ ኢትዮጵያዊያን ህገ-ወጥ የሰው አዘዋዋሪዎች በዝውውሩ ሂደት የሚያደርሱባቸውን እንግልትና አደጋ በመጋፈጥ በሳውዲ አረቢያ፣ የመን፣ ባህሬን እና ሌሎች የመካከኛው ምስራቅ ሃገራት ያለውን የስራ እድል እየተጠቀሙ ይገኛሉ፡፡ በየመን ህገ-ወጥ የሰው አዘዋዋሪዎች ከስደተኞቹ ቤተሰቦች ከፍተኛ መጠን ያለው የካሳ ገንዘብ ለመቀበል ሲሉ ስደተኞቹን አግተው ያቆይዋቸዋል፡፡ በ2013 ዓ.ም. ማገባደጃ እና በ2014 ዓ.ም. መጀመሪያ በመቶ ሺዎች የሚቆጠሩ እና በአብዛኛው ኢትዮጵያዊያን የሆኑ ስደተኛ ሰራተኞች በሳውዲ አረቢያ ታግተው ወደ ኢትዮጵያ እንዲመለሱ ተደርጓል፡፡ የሳውዲ አረቢያ የጸጥታ ሃይል እና መደበኛ ዜጎች ኢትዮጵያዊያኑ ላይ ጥቃት ፈጽመዋል፤ በዚህም ምክንያት  ወደ ተወሰኑ ሃገራት ለስራ የሚደረጉ ጉዞዎች ላይ እገዳ ተጥሏል፡፡

በሃይል ማፈናቀል
የኢትዮጵያ መንግስትም ሆነ ለጋሽ ማሕበረሰቡ ከሰፈራ መርሃ-ግብር ጋር በተያያዘ ተፈጽመዋል የተባሉትን በደሎች ተገቢ በሆነ መልኩ ማጣራት ሳያደርጉ ቀርተዋል፡፡ በዚህ መርሃ-ግብር መሰረታዊ አገልግሎቶቻቸውን ለማሟላት በሚል ምክንያት 1.5 ሚሊዮን ሰዎችን እንደ አዲስ ለማስፈር ዕቅድ ተነድፎ ነበር፡፡ በመርሃ-ግብሩ የመጀመሪያ ዓመት የተካሄዱ አንዳንድ የመልሶ ማስፈር ስራዎች በጋምቤላ ክልል የሃይል እርምጃን ያስከተሉ ሲሆን ይህም ድብደባ፣ የዘፈቀደ እስር፣ እና በቂ ያልሆነ ሰፋሪዎችን የማሳመን ስራ እና የካሳ ክፍያን ይጨምራል፡፡

በ2013 ዓ.ም. ኢትዮጵያዊያን ለዓለም ባንክ የቁጥጥር ፓነል የድርጅቱን ገለልተኛ የተጠያቂነት አሰራር በተመለከተ ያቀረቡት አቤቱታ በምርመራ ላይ ይገኛል፡፡ ኢትዮጵያዊያን ስደተኞች በጋምቤላ ክልል ነባር ነዋሪዎችን ያለፈቃዳቸው በማፈናቀል የተካሄደውን ብሄራዊ የሰፈራ መርሃ-ግብርን በተመለከተ ባንኩ የራሱን ፖሊሲዎች ጥሷል በሚል ቅሬታ አቅርበዋል፡፡ በሐምሌ ወር የዩናይትድ ኪንግደም ፍርድ ቤት የሃገሪቱ ዓለምዓቀፍ ተራድኦ ድርጅት (UK Department for International Development (DFID)) በሰፈራ መርሃ-ግብሩ ሂደት ላይ ደርሰዋል የተባሉ  የሰብዓዊ መብት ጥሰቶችን በተመለከተ የቀረበውን ማስረጃ በትክክል አልመረመረም በሚል የቀረቡ ክሶች መደበኛ የፍርድ ቤት ምርመራ ይደረግባቸዋል በማለት ወስኗል፤ ይህ የፍርድ ቤት ምርመራ ሂደት ይህ ሪፖርት እየተዘጋጀ በነበረበት ወቅት ገና አልተጀመረም።

ኢትዮጵያ በታችኛው ኦሞ ሸለቆ የስኳር ልማት ተከላ በማካሄድ ላይ ትገኛለች፤ ይህም የሚከናወነው 245 ሺህ ሄክታር የሚሆን የ200 ሺህ ነባር ነዋሪዎች መሬትን በማጽዳት ነው፡፡ ነባር ነዋሪዎች ያለ በቂ የማሳመን ስራ እና ካሳ ሳይከፈላቸው በመፈናቀል ላይ ይገኛሉ፡፡ በመንግስት ለሚተዳደረው የስኳር ልማት ተከላ ሲባል የነባር ነዋሪዎቹ የግጦሽ መሬቶች  እየተመነጠሩ ሲሆን ነዋሪዎቹ ሰብል ለማብቀል ከኦሞ ወንዝ ያገኙ የነበረው ውሃ ላይ ገደብ ተደርጓል፡፡ የልማት እቅዱን በተመለከተ ጥያቄ ያቀረቡ ግለሰቦች ለእስር እና ማሳደድ ይዳረጋሉ። ጉዳዩን ለመዘገብ የፈለጉ የሃገር ውስጥ እና የውጭ ጋዜጠኞች ኦሞ ሸለቆ እንዳይደርሱ እግድ ተጥሎባቸዋል፡፡

የተመሳሳይ ጾታ ግንኙነት መብት
የኢትዮጵያ የወንጀል ሕግ ለአካለ መጠን በደረሱ ሰዎች መካከል በስምምነት የሚደረግን ተመሳሳይ ጾታዊ ግንኙነት እስከ 15 ዓመት በሚደርስ እስራት ይቀጣል፡፡ በመጋቢት ወር የኢትዮጵያ ፓርላማ አባላት ተመሳሳይ ጾታዊ ግንኙነት ይቅርታ የማያሰጥ ወንጀል ሆኖ እንዲነገግ ሀሳብ አቅርበው ነበር፤ ይህም በዚህ ወንጀል ጥፋተኛ የሆኑ እስረኞች ከተፈረደባቸው የእስር ጊዜ አስቀድመው እንዳይወጡ የሚያግድ ነው፡፡ ሆኖም መንግስት በሚያዚያ ወር የቀረበውን የህግ ማሻሻያ ሃሳብ ውድቅ አድርጎታል፡፡

ኢትዮጵያ በተባበሩት መንግስታት ድርጅት የሰብአዊ መብቶች ምክር ቤት ለሚካሄደው ዩኒቨርሳል ፒርዮዲክ ሪቪው (Universal Periodic Review) ግምገማ በግንቦት ወር 2014 ዓ.ም. ቀርባ ነበር፤ በዚህ ግምገማ ላይ የተመሳሳይ ጾታዎች ግንኙነት የወንጀል ድርጊት መሆኑን እንድታስቀር እና ጾታዊ ግንኙነትን መሰረት ባደረገ መልኩ የሚደረግን አድልዎ እንድታስቆም የቀረቡላትን ምክረ ሃሳቦች በሙሉ ውድቅ አድርጋለች።

ዋና ዋና ዓለምዓቀፍ አካላት
ኢትዮጵያ ጥያቄ የማይቀርብበት የውጭ ለጋሾች ዕርዳታና  የአብዛኞቹ የጎረቤት ሃገራትን ድጋፍ ማግኘቷን ቀጥላለች፤ ይህም የአፍሪካ ህብረት መቀመጫ በመሆኗ ባላት ሚና፣ ለተባበሩት መንግስታት የሰላም ማስከበር ተልዕኮ በምታበረክተው ሃይል፣ ከምዕራብያዊያን ሃገራት ጋር ባላት የደህንነት እና የእርዳታ ትብብር እንዲሁም ሃገሪቱ በልማት መለኪያዎች አሳይታለች በሚባለው እድገት ላይ የተመሰረተ  ነው።

ኢትዮጵያ ታላቁን የህዳሴ ግድብ መገንባት በመጀመሯ ሳቢያ ከግብጽ ጋር ያላት ግንኙነት ሻክሯል፤ግድቡ የናይል ውሃ ወደ ግብጽ የሚያደርገውን ፍሰት የሚቀለብስ ሲሆን በ2018 ዓ.ም. እንደሚጠናቀቅ ይጠበቃል፡፡ በ2014 ዓ.ም. ኢትዮጵያ በጦርነት ላይ የሚገኙ የደቡብ ሱዳን አካላትን አደራድራለች፤ ወታደሮቿም ውዝግብ ያለበትን የአቢዬ ግዛት ማረጋጋት ችለዋል። የኢትዮጵያ ጦር ሃይል ወደ ሶማሊያ  ዘልቆ መግባቱን የቀጠለ ሲሆን በጥር ወርም የአፍሪካ ህብረትን የሰላም አሰከባሪ ሃይል ተቀላቅሏል፡፡

ኢትዮጵያ በአፍሪካ ከፍተኛ እርዳታ ከሚቀበሉ ሃገሮች አንዷ ናት፤ በ2014 ዓ.ም. 4 ቢሊዮን  የአሜሪካን ዶላር የሚጠጋ እርዳታ ተቀብላለች፤ ይህም ወደ 45 በመቶ የሚሆነውን የሀገሪቱን ዓመታዊ በጀት ይሸፍናል፡፡ ለጋሾች የኢትዮጵያን የሰብዓዊ መብት አያያዝ በተመለከተ ድምጽ አያሰሙም፤ ተፈጽመዋል የተባሉ በደሎችን በተመለከተ ለማጣራት ብዙም ትርጉም ያለው እርምጃ አልወሰዱም። የዓለም ባንክን ጨምሮ ለጋሾች የሚሰጡት የልማት እርዳታ በሃገሪቱ ላለው የሰብዓዊ መብቶች ችግር አስተዋጽኦ አለማድረጉን ወይም ችግሩ እንዲባባስ አለማገዙን ለማረጋገጥ የሚያስችሉ እርምጃዎችን እስካሁን አልወሰዱም።

በግንቦት ወር የሃገሪቱ Universal Periodic Review/ግምገማ በተካሄደበት ወቅት በርካታ ሃገራት ኢትዮጵያ የበጎ አድራጎት ድርጅቶች እና ማህበራት አዋጅን እና የጸረ-ሽብር አዋጅን እንድታሻሽል ያቀረቡትን ምክረ ሃሳብ ውድቅ አድርጋዋለች፡፡