Skip to main content

ኤርትራ

Events of 2018

Eritrea's President Isaias Afwerki arriving at the airport in Gondar, for a visit in Ethiopia, November 9, 2018.

© 2018 EDUARDO SOTERAS/AFP/Getty Images

ከአስርት አመታት ዲፕሎማሲያው መገለል በኋላ 2018 ኤርትራ ከጎረቤቶቿ ጋር ያላት ግንኙነትን ላይ ጉልህ የሆነ ለውጥ ያመጣችበት አመት ነው። በሃምሌ ወር ኤርትራ ከሃያ አመት በፊት የተጀመረውን የድንበር ጦርነት በይፋ ስታቆም የኤርትራና የኢትዮጵያ መሪዎች “የአዲስ ዘመን ሰላምና ወዳጅነት” ለማጎልበት ባለ አምስት ነጥብ መግለጫ አውጥተዋል። ከአንድ ወር በኋላ ኤርትራና ሶማሊያ ከ20 አመት በኋላ የዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት እንደገና የጀመሩ  ሲሆን  ጅቡቲና ኤርትራም ወዲያውኑ የዲፕሎማሲያዊ ግንኙነታቸውን ቀጥለዋል። በህዳር ወር የተባበሩት መንግስታት በኤርትራ ላይ የጣለውን ዘጠኝ አመት  የቆየውን የጦር መሳሪያ እገዳ አንስቷል። ከነዚህ ሁሉ ለውጦች በኋላም ኤርትራ መሰረታዊ መብቶች ላይ የምታካሂደውን አስከፊ ጭቆና ለማቆም ምንም ምልክት አላሳየችም።

ፕሬዝዳንት ኢሳያስ አፈወርቂ ለሁለት አስርተ አመታት ከኢትዮጵያ ጋር የነበርውን አለመስማማት አምባገነናዊ ስርአታቸውን ለማቆየት ተጠቅመውበታል። የብሄራዊ አገልግሎትን ህጉ በ18 ወራት ቢገደብም የግዳጅ ምልምሎች ግን ያለ ጊዜ ገደብ እንዲቆዩ ይገደዳሉ። የኢሳያስን አገዛዝ የሚቃወሙ ማንኛውም የፖለቲካ ተቀናቃኞች ፍርድ ቤት ሳይቀርቡ ካለገደብ አብዛኛው ጊዜ ማንንም በማያገኙበት ሁኔታ ወህኒ እንዲወርዱ ተደርጓል። ነፃ የመገናኛ ብዙሃን የተከለከሉ ሲሆን ጋዜጠኞችም ለእስር ተዳርገዋል። የፖለቲካ ፓርቲዎችና መንግስታዊ ያልሆኑ ድርጅቶችም የተከለከሉ ሲሆን ምርጫ፥ ህግ አውጭ እና ገለልተኛ የፍትህ ስርአት የኤርትራን የመከላከያ አቅም ያዳክማል ብለው ኢሳያስ ይከራከራሉ። አንዳንድ የሃይማኖት ቡድኖች ከነጭራሹ የታገዱ ሲሆን ሌሎቹ ደግሞ በመንግስት ተሿሚዎች ከፍተኛ  ቁጥጥር ይደረግባቸዋል። ከጦርነቱ በፊት በ1997 በተመራጮች ስብስብ የፀደቀውን ህገመንግስት በተግባር ላይ እንዳይውል ችላ ተብሏል።

ከኢትዮጵያ ጋር የተፈጠረው መግባባት የኢሳያስን አፋኝ ህጎች ሰበብ ያሳጣ ቢሆንም የአገዛዙን አስከፊነት ግን አልቀነሰውም:: ከኤርትራና ኢትዮጵያ መግለጫ ሁለት ሳምንት ቀድሞ የወጣው የተባበሩት መንግስታት የሰብአዊ መብት መግለጫ ሁኔታውን ያጠቃለለው  “ስርአትን የተከተለ፤  መጠነ ሰፊ ፥አስከፊ የመብት ጥሰት ነው" ይህም ፍፁም “ከተጠያቂነት ነፃ በሆነ” ሁኔታ የተፈፀመ ነው በማለት ነው:: በኤርትራ ላይ የወጣው ራፖር እንዳመለከተው ከተፈፀሙት የመብት ጥሰቶች " የጅምላ እስር: የሰው ደብዛ ማጥፋት: ማሰቃየት: ወሲባዊ ጥቃት እና የጉልበት ብዝበዛ" እና የመሳሰሉት ይገኙበታል:: የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር በተለመደው ለትችቶች መልስ በሚሰጥበት ቃና ይህንንም መግለጫ " ስነ ምግባር የጎደለው፥ ሀቅን ሆን ብሎ ያጣመመ እና ብልሹ የሆነ አጀንዳ ማራመጃ ነው" በማለት አጣጥሎታል:: 

በአመቱ መጨረሻ ላይ እንደታየው ምንም የተለወጠ ሁኔታ ባይኖርም በጥቅምት ወር የተባበሩት መንግስታት አጠቃላይ ጉባዔ ኤርትራን ለሰብዓዊ መብት ጉባዔ ምክር እንድትመረጥ አድርጓል። 

ገደብ የለሽ የውትድርና አገልግሎት እና የጉልበት ብዝበዛ

ኤርትራ የዜጎቿ አጠቃላይ መብት በከፍተኛ ሁኔታ የተገደበ ቢሆንም የጊዜ ገደብ የሌለው ብሄራዊ አገልግሎት እና ጉልበት ብዝበዛ በተለይም ወጣቱን ካለፍቃድ ለብሄራዊ አገልግሎት እንዲዘምት  እያደረገና እየጎዳው ይገኛል:: በ2017  የወጣው የተባበሩት መንግስታት የሰብዓዊ መብት ጥሰት አጣሪ  ኮሚሽን መግለጫ ላይ ብሄራዊ አገልግሎቱን "ባርነት" ነው ብሎ ሲገልፀው ኤርትራ ከኢትዮጵያ ጋር ስምምነት ፈፅማ እንኳ  ለረጅም ጊዜ ብሄራዊ አገልግሎት ላይ የቆዩ የግዳጅ ዘማቾችን እስካሁን እንዳላስናበተችም አክሎ ገልፆል:: 

18 አመት የሞላው ስው ሁሉ ለብሄራዊ አገልግሎት በግዳጅ ይመለመላል :: ብሄራዊ አገልግሎቱ ጠባቂ የሌላቸው ህፃናትና ጨምሮ በየወሩ ለሚሰደዱ በሺህ ለሚቆጠሩ ኤርትራውያን ብቸኛው ምክንያት ባይሆንም ዋነኛው ግን እንደሆነ ይታመናል።  ከ1998  ጦርነት ጀምሮ 15 በመቶ ያህሉ ህዝብ ለስደት ተዳርጏል:: እንደ የተባበሩት መንግስታት የስደተኞች ከፍተኛ ኮሚሽን መግለጫ ከኤርትራና ኢትዮጵያ ድንበር መከፈት በኃላ የስደተኞች ቁጥር ጠባቂ የሌላቸውን ህፃናቶች ጨምሮ በከፍተኛ ሁኔታ  አሻቅቧል::

የብሄራዊ አገልግሎት ምልምሎች ካለ ምንም መፍትሄ ማሰቃየትን ጨምሮ ከፍተኛ የሆነ ኢ-ሰብአዊ እና ክብረ ነክ ቅጣቶች ይደርስባቸዋል:: ከቅርብ አመታት ወዲህ የደሞዝ ጭማሪ ቢደረግላቸውም ለምግብ የሚቆረጥባቸው በዛው ልክ በመጨመሩ የሚከፈላቸው ገንዘብ በጣም ትንሽ በመሆኑ ቤተሰብ ለመርዳት እንኳ በቂ አልሆናቸውም:: 

የትምህርት ሚኒስትሩ በ2018 ባደረጉት ቃለመጠየቅ ላይ ለብሄራዊ አገልግሎት በግዳጅ ከሚመለመሉት ውስጥ ከአንድ አምስተኛ የሚያንሱ ብቻ ወታደራዊ ሚና እንዳላቸው አምነዋል። የተቀሩት የእርሻ ጉልበት ስራ ላይ የተስማሩ፥ አስተማሪዎች፥ የግንባታ ሰራተኞች፥ የቢሮ ሰራተኞች፥ ዝቅተኛ ደረጃ ላይ ያሉ ዳኞች እና ሌሎች አይነቶች የጉልበት ስራ ላይ የተሰማሩ ናቸው። የግዳጅ ምልምሎችን በመንግስት በሚተዳደሩ የግንባታ ድርጅቶች በመመደብ ባለቤትነቱ የውጭ ዜጋ የሆነ  የማእድን አውጭ ኩባንያ ግንባታ እንዲሰሩ ይደረጋሉ።

የመማር መብት

የኤርትራ መንግስት የሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶችን በሺህ የሚቆጠሩ ወጣቶችን ለብሄራዊ አገልግሎት መመልመያነት ሲጠቀምበት ተማሪዎቹ የሁለተኛ ደረጃ ትምህርት የመጨረሻ አመት ወደ አስከፊው ሳዋ ወታደራዊ ካምፕ ሄደው እንዲያሳልፉ ያስገድዳል። በአግባቡ የሰለጠኑና ፍቃደኛ አስተማሪዎችን ከማፍራት ይልቅ መንግስት በግዳጅ ምልምል ብሄራዊ አግልግሎት ሰጪዎች ላይ ተስፋ ማድረግን የመረጠ ሲሆን የግዳጅ ምልምሎችም ስለሚመደቡበት ሁኔታ እንኳን ምንም አይነት  ምርጫ የማይሰጣቸውና፤ ግዳጃቸውም መቼ እንደሚያበቃ የሚያውቁት ነገር የለም።

ለአስርት አመታት የዘለቀው የግዳጅ ዘመቻ ብቃትም ሆነ ፍላጎት የሌላቸውን ምልምሎች አስተማሪ በማድረጉ የተተኪ ወጣት ኤርትራውያንን የመማር መብት እየጎዳ ይገኛል። በቂ ባልሆነ ደሞዝ እና ገደብ የለሽ አገልግሎት የተነሳ አስተማሪዎች ከማስተማር ገበታቸው የሚቀሩ ሲሆን አብዛኛዎቹም ይሰደዳሉ። ተማሪዎቹም በደካማ የትምህርት አሰጣጥ ምክንያት ተነሳሽነት የሌላቸው ሲሆን ማለቂያ በሌለው የግዳጅ ብሄራዊ አገልግሎት የተነሳ ደግሞ የመማር ጥቅሙ አንሶ ይታያቸዋል።

የመናገር፤ሃሳብን የመግለፅ እና የመሰብሰብ መብት

በ1993 መንግስት የግል መገናኛ ብዙሃንን ካጠፋና 10 ጋዜጠኞችን ካለምንም የፍርድ ቤት ሂደት ያለገደብ ካሰረ በኋላ ስራቸውን እንዲቀጥሉ ፍቃድ የከለከለ ሲሆን መንግስታዊ ያልሆኑ ድርጅቶችም እንዲንቀሳቀሱ አልተፈቀደላቸውም።

መንግስት ከ2001 ጀምሮ ያሰራቸውን ታዋቂ እስረኞች፥ የመንግስት ባለስልጣናት እና ጋዜጠኞች ያልፈታ፥ ያሉበትንም ሁኔታ ያላሻሻለ ሲሆን እስካሁንም በማንም መጎብኘት በማይችሉበት ሁኔታ ታስረው ይገኛሉ። መንግስት ግልፅ ባለመሆኑ ምክንያትና  ምንም አይነት  ገለልተኛ ተቆጣጣሪ አካል በሌለበት ሁኔታ ምን ያህል የፖለቲካ እስረኞች እንዳሉ ለማወቅ አዳጋች ሆኗል።

መንግስት በመጋቢት ወር የ90 አመቱን አል ኢድ የሚባለው የግል የእስልምና ትምህርት ቤት የክብር ፕሬዝዳንትና በ2017 ጥቅምት ወር የመንግስት ትምህርት ቤቱን የመውረስ እቅድ ሲቃወሙ የታሰሩትን ግለሰብ አስከሬን አስረክቧል። በአስመራ የቀብሩን ስነስርአት ለመከታታል የወጡ በሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎች ህፃናትን ጨምሮ ለእስር ተዳረገዋል። አብዛኛዎቹ ታሳሪዎች በ3 ወር ጊዜ ውስጥ ከእስር የተፈቱ ሲሆን የተወሰኑ የትምህርት ቤት መሪዎች ግን ይህ ሪፓርት እስከወጣበት ጊዜ ድረስ አልተፈቱም።

የቀድሞ የገንዘብ ሚኒስትር የነበሩትና የፕሬዝዳንቱ ተቺ ብርሃኔ አብረሃ መስከረም ወር ላይ ሲታሰሩእስከአሁን ግን የት እንዳሉ አይታወቅም። ብርሃኔ የኢሳያስን አገዛዝ ችግሮች በዝርዝር የሚያብራራ መፅሃፍ አሳትመው የነበረ ሲሆን ወጣቱን በስርአቱ ላይ እንዲያምፅ ጥሪ አድርገዋል። መንግስት የብርሃኔ ባለቤት የሆኑትን አልማዝ ሃብተማርያም በጥር ወር ላይ ሲያስር እስከአሁን ድረስ በማንም እንዲጎበኙ አልተፈቀደም።

የእምነት ነፃነት

መንግስት ከሱኒ ኢስላም፥ የኤርትራ ኦርቶዶክስ፥ የሮማ ካቶሊክ እና የሉትራን ኢቫንጄሊካል ቤተክርስትያን ውጭ ያሉ እምነቶችን እውቅና መስጠት አይፈልግም። የኤርትራ ኦርቶዶክስ ፓትርያርክ አንቶኒዮስ በ2007 በመንግስት ማዕረጋቸው ከተነጠቁ  በኋላ በቁም እስር ላይ ይገኛሉ።

የደህንነት ሃይሎች ያልተፈቀደ እምነት አማኞች ለጋራ ፀሎት የሚገናኙባቸውን ቤቶች ድንገቴ ወረራ ያካሄዱባቸዋል። ከእስር ለመፈታትም የሚከፍሉትም ዋጋ እምነታቸውን መካድ ነው። በመጋቢት ወር አዲስ ሙሽሮች ከሰርጋቸው ፕሮግራም ጋር በተያያዘ እንዲታሰሩ ተደርገዋል።  

በ1994 የተያዙትን ሶስት ሰዎች ጨምሮ ሃምሳ ሶስት የጆቫ ምስክሮች ታስረው ወደ ሳዋ ወታደራዊ ማሰልጠኛ እንዲላኩ ተደርጏል። በ2017 ወደ ማኢ ሰርዋ እስር ቤት ከተላኩ በኋላ የአያያዛቸው ሁኔታ መጠነኛ ለውጥ አሳይቷል። ከታሰሩ ጀምሮ ለመጀመሪያ ጊዜ ለአጭር ወቅት ጎብኚ የተፈቀደላቸው ቢሆንም በ2018 መጨረሻ ላይ በድጋሚ ታግዷል።

ስደተኞች

ከኢትዮጵያ ጋር በተፈጠረው መልካም ግንኙነት የተነሳ ኤርትራውያን ስደተኞች ከአንዳንድ በስደት ከሚኖሩባቸው ሃገሮች ወደ ሃገራቸው እንዲመለሱ ሊደረግ የሚችልበት እድል አለ። ኢትዮጵያ የኤርትራ ተቃዋሚዎችን መንቀሳቀሻ የዘጋች ቢሆንም በሃገሪቱ ውስጥ የሚኖሩ አንድ መቶ ስልሳ አራት ሺህ ስደተኞች ለማባረር የወሰደችው ምንም እርምጃ ግን የለም።

እስራኤል የኤርትራና የሱዳን ስደተኞችን “ሰርጎ ገቦች” በማለት የተደጋገመ ከባድ ጫናዎች በመፍጠር “በፈቃደኝነት” ሃገር ለቀው እንዲወጡ እየገፋቻቸው ትገኛለች። በጥር ወር የእስራኤል ባለስልጣናት ስደተኞቹ ወደ ሩዋንዳ ወይንም ኡጋንዳ የማይሄዱ ከሆነ ያለምንም ጊዜ ገድብ እንደሚታሰሩ ተናግረዋል። ሶስተኛ ሃገሮች ማንኛውም ከእስራኤል የተባረረን ሰው እንደማይቀበሉ ካሳወቁ በኋላ በመጋቢት ወር ላይ የእስራኤል ፍርድ ቤት ፖሊሲውን ህገወጥ በማለት ውድቅ አድርጏታል። የእስራኤል ፍትህ ሚኒስትር ኤርትራ ብሄራዊ አገልግሎቱን ከሰረዘች ስደተኞቹን ወደ ሃገራቸው መመለስ የማይቀር ነው ብለዋል።

በመስከርም 2017 አሜሪካ የፖለቲካ ጥገኝነት የተከለከሉ ሰባት መቶ ኤርትራውያን ወደ ሃገራቸው እመልሳለሁ ብላለች። አንዳንዶቹ ወደ ካናዳ አምልጠዋል። አንድ ግለሰብ ደግሞ ወደ ሃገሩ በመመለስ ላይ እያለ ካይሮ አውሮፕላን ማረፊያ ላይ እራሱን አጥፍቷል።

መስከረም ወር ላይ የስዊዝ የፌዴራል አስተዳደር ፍርድ ቤት ከሃገር ማባረሩ ህገ ወጥ ነው እንዳይባል የኤርትራ ብሄራዊ አገልግሎት እንደሚባለው አስከፊ አይደለም በማለት መመሪያ አፅድቋል። የ2017ቱ የአውሮፓ የፖለቲካ ጥገኝነት ድጋፍ ቢሮ መግለጫ ወደ ኤርትራ በግዳጅ የተመለሱ ኤርትራውያኖች ለቅጣት እንደሚጋለጡና ቅጣቶቹም ኢሰብአዊ በሆነ ሁኔታ መታሰር፥ የጉልበት ብዝበዛ እና ማሰቃየት እንደሚደርስባቸው ቢገልፅም የስዊዝ ፍርድ ቤት ግን መመሪያውን ከማፅደቅ ወደኋላ አላለም።

ዋና ዋና አለም አቀፍ ተዋናዮች

ኤርትራ ከኢትዮጵያና ሶማሊያ ጋር የቀጠለችው ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት ኤርትራ አልሸባብን በመደገፏና ጅቡቲን በመውረሯ የተጣለባት የመሳሪያ እገዳ እንዲነሳ ሁለቱም ሃገሮች ድጋፍ እንዲያደርጉላት አግዟታል። ጅቡቲ ከኤርትራ ጋር ያላት የድንበር ጭቅጭቅ እልባት ያላገኘ በመሆኑና ኤርትራ ደብዛቸው ለጠፋ የጦር ምርኮኞች ሃላፊነት ያልወሰደች በመሆኑ ማዕቀቡ መነሳቱ ላይ እያንገራገረችም ቢሆን ተስማምታለች። 

ከጀርባ በመሆን የኤርትራንና ኢትዮጵያን የስላም ድርድር ያመቻቹት የተባበሩት አረብ ኢምሬትስ  ለየመኑ የእርስ በርስ ጦርነት መገልግያነት የሚሆን ለአሰብ ወደብ ቅርብ የሆነ ወታደራዊ ካምፕ የተከራዩ ሲሆን ከኢትዮጵያ ጋርም አሰብን ከአዲስ አበባ ጋር የሚያገናኝ የነዳጅ ማስተላለፊያ መስመር ለመዘርጋት መስማማታቸውን አሳውቀዋል። በመስከረም ወር ሩሲያ ኤርትራ ወደብ ላይ የሎጀስቲክ ማዕከል የመገንባት እቅድ እንዳላት ያሳወቀች ቢሆንም ስለ ፕሮጀክቱ ዝርዝር ሁኔታ ግን ምንም ያለችው ነገር የለም።

በአሜሪካ ወጭ ጉዳይ ሚኒስቴር መስሪያ ቤት የአፍሪካ ጉዳዮች ተጠባባቂ ረዳት ሚኒስትር  አምባሳደር ዶናልድ ያማማቶ በሚያዚያ ወር ኤርትራን ጎብኝተዋል። ከአምባሰደሩ ጉብኝትም ሆነ  ከኢትዮጵያ ስምምነት በኋላ ከ2001 ጀምሮ ለእስር የዳረገቻቸውን የአሜሪካ ኤምባሲ ሰራተኞች በእስር ቤት ውስጥ ማቆየቷን ቀጥላለች።

የቻይና ኩባንያዎች በኤርትራ የማእድን ዘርፍ ላይ ጉልህ የሆነ የመዋለ ንዋይ ፍሰት ማድረጋቸውን ቀጥለዋል። የማእድን ማውጫዎቹ ለሚያካሄዱት ግንባታዎች በመንግስት የሚተዳደሩ የግንባታ ድርጅቶችን የመጠቀም ግዴታዎች ያሉባቸው ሲሆን በተዘዋዋሪ ከግዳጅ ዘማቾች ጉልበት ብዝበዛ እንዲያተርፉ ይደረጋል። በቢሻ የሚገኝ አንድ ማእድን ማውጫ ከፍተኛውን ድርሻ  ለረጅም ጊዜ የካናዳው ኔቭሱን ማእድን የተያዘ ነበር። በመስከረም ወር ግን ኔቭሱን ማእድን ለቻይናው ዚጂንግ ማእድን ማውጫ ለመሸጥ ተስማምቷል። ሽያጩ በህዳር ወር የካናዳ እና የቻይና ህጋዊ እና የቁጥጥር መስፈርቶችን አልፏል ።